ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ማሰብን ከመስቀሉ ስራ እየተማርን መለወጥ ያስፈልገናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

179

መስከረም 16 / 2015(ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓልን በምናክብርበት ወቅት ከጥላቻ ፍቅርን፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ማሰብን ከመስቀሉ እየተማርን መለወጥ ያስፈልገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ በመዲናዋ እየተከበረ በሚገኘው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በሀገራችን ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ብዙ መልኮች ያለው ሲሆን ፍቅር የሚገለጽበት፣ ወዳጅነት የሚጠነክርበት፣ አብሮነት የሚያብብበት፣ አንድነት የሚጎለብትበት ህዝባችንን ያስተሳሰረ ያቀራረበ ትልቅ ሚና የተጫወተ በዓል ነው ብለዋል።

መስቀል እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሁሉ ያለ ዘር፣ ያለ ቀለም ያለ ጾታ ያለ ሀይማኖት እና ምንም ልዩነት መውደዱን ህይወቱን በመስጠት ወደር የማይገኝለትን ፍቅር የገለጸበት ምልክት ነው ብለዋል።

የሰው ልጅ እውነተኛ ፍቅርን ከእየሱስ ክርስቶስ ስራ መማር ቢችል በዓለም ላይ ፈታኝ የሆኑ ብዙ ነገሮች መፍትሄ ሊያገኙ ይችሉ ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሀገራችንም ይህንን ፍቅርን መተሳሰብን ከእያዳንዳችን ከልጆቿ ትፈልጋለች ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንገድ መስቀሉን ለመደበቅ የተደረገውን ታሪክ የሚመስል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃባቷ እንዳትጠቀም የሚሰነዘሩ ብዙ የክስ ውርጅብኝ በፍትሃዊነት ለማሸነፍ እየጣረች ያለች ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና ሁሉ እያሸነፈች በጽናት እንደምትቀጥል እናምናለን መስቀል፣ የፍቅር፣የሰላም የአብሮነት በዓል ነው ያሉት።

ይህንን በዓል ስናከብር በፍቅር በመተሳሰብ ለዘላቂ ሰላም እየሰራን፣ጀግኖቻችንን እያከበርን አንድነታችንን እያጸናን መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።