ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር 73 ሚሊየን ለማድረስ አቅዷል

96

አዲስ አበባ መስከረም 16/2015 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት የደንበኞችን ቁጥር 73 ሚሊየን ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም የቀጣይ ሶስት ዓመት የዕድገት  ስትራቴጂ ና የ2015 በጀት ዓመት የስራ እቅዱን በዛሬው እለት ለመገናኛ ብዙሃን አስተዋውቋል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኩባንያው ባለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ብሪጅ የተሰኘ የሶስት ዓመት የዕድገት ስትራቴጂ ቀርፆ ሲተገብር መቆየቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ “ሊድ” የተሰኘና ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር አዲስ ዕድገት ስትራተጂ ቀርዖ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ስትራቴጂው በኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩ እድገትና ለውጦችን እንዲሁም ከውድድር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከነባረዊ ሁኔታዎች ጋር ታሳቢ በማድረገ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ከኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር የዲጂታል አገልግሎቶች በማቅረብ ድርጅቶችን እንዲሁም ግለሰቦችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥ አካታች እድገት እንዲኖር የማስቻል ራዕይ የሰነቀ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ስትራቴጂው በውድድር ገበያ የመሪነት ሚና በመጫወት ተቋሙ በማኀበረሰቡ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲኖረው የማስቻል ታላቅ ዓላማን ያነገበ እንደሆነም የገለፁት።

በዚህም በቀጣይ ሶስት ዓመት አስተማማኝ የኮሙዩኒኬሽንና የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት በማቅረብ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማፍጠን ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከሶስት አመት ስትራቴጂ የተቀዳ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

ዕቅዱ የደንበኞችን እርካታ የሚያሳድጉና ተሞክሮ የሚያሻሽሉ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል ነው ።

በበጀት ዓመቱ የገበያን ድርሻ ማስጠበቅ የሚያስችሉ የኔትወርክና ሲስተም አቅም ማሳደግ እና አዳዲስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ይተገበራሉ ብለዋል።

ኩባንያው በ2015 በጀት አመት 8 ሚሊየን ተጨማሪ ደንበኞች ማስተናገድ የሚችል ኔትወርክ አቅም በመገንባት የደንበኞችን ቁጥር 73 ሚሊየን ለማድረስ ማቀዱን ተናግረዋል።

የገቢ መጠኑን በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 61 ቢሊዮን ብር 22 በመቶ በማሳደግ 75 ቢሊዮን ብር ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

ኩባንያው የአገልግሎት አይነቶችን በማሳደግና በማሻሻል የደንበኞችን እርካታ ፣ቆይታንና ታማኝነትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም