መስቀል ደመራ - የመስከረም ደማቅ መልክ ማሳያ

479

(አየለ ያረጋል)

  • መስከረም ሁለንተናዊ ውበቱ ድንቅ ነው፤ ትዕምርቱም ጉልህ ነው፤ የወራት ቁንጮው መስከረም ደማቅ መልኮች መካከል አንዱ ደመራ፤ በዓለ መስቀል ነው።
  • ከደመራው ዓመድ ልጆች ግንባራቸው ላይ የመስቀል ምልክት በማድረግ የዛሬ ዓመት አድርሰኝ ስለት ይሳላሉ።
  • መስቀል የወል ክብረ በዓል ነው፤ የጋርዮሽ አከባብር። በዚህ ዕለት የግድ በዓሉን በጋራ ማክበር ስለሚያስፈልግ የተጣላ ጎረቤት ሁሉ ይታረቃል።

በኢትዮጵያ ዘመን ቆጠራ ቀለበት ውስጥ ወርኅ መስከረም ተናፋቂ ነው። ሊቃውንት መስከረምን ሲፈትቱት መስ- 'ዐለፈ፤ ከረመ' ይሉትና 'ክረምቱን ማስከረሚያ፤ የጥቢ መባቻ" ወርኅ ሲሉ ያመሰጥሩታል። ደራሲ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር “ቀዳማይ፣ ርዕሰ ክራሞት፣ መቅድመ አውርኅ፣ ርዕሰ ዐውደ ዓመት፣ የክረምት ጫፍ መካተቻ፣ የመፀው መባቻ” ይሉታል ወርኃ መስከረምን። እናም ዘመነ ማዕዶቷን፤ ወርኅ ተውሳኳን ‘ጳጉሜን’ ተሻግሮ መስከረምን መሳም ይጓ'ጓ'ል። የመስከረም ጥባት በአያሌው ይሻታል። መስከረም የወራት ሁሉ ቁንጮ ይመስላል። መስከረም ዘመን ያስረጃል፤ አዲስ ሕይወትና ተስፋ ደግሞ ይደግሳል።

የባህር ሐሳብ ሊቃውንት መስከረም 1 ቀን ዓለም የተፈጠረበት፤ ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ ውሃው መጉደሉን ለማረጋገጥ ወደ ምድር የላካት እርግብ ቅጠል ይዛ የተመለሰችበት፣ እስራኤላዊያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ ቀይ ባሕርን የተሻገሩበት የብስራት ዕለት እንደሆነ ያነሳሉ። በእነዚህና ሌሎች ኃይማኖታዊ ትውፊቶች ከጥንት ጀምሮ ነው መስከረም ለዘመን መለወጫነት የተመረጠው' ይላሉ። ዕለቱም ‘ርዕሰ ዓውደ ዓመት’ ይሉታል።

መስከረም ለመልክዓ ምድሩ፣ ለሰውና ለእንስሳት ሁሉ ‘ፍስኃ ወተድላ’ በማለት የደስታና የተድላ ወር ነው። በመስከረም ምድር ትረጋለች፣ በአበቦች ታጌጣለች፣ በእንቁጣጣሽ ትፈካለች። ውኆች ይጠራሉ። በሰማዩ ላይ ሰማያዊ ብርሃን ይወጣል፤ የጥቁር ደመና ጋቢ ይገፈፋል፤ ክዋክብት በሰማይ ብረት ምጣድ ላይ መፈንጨት ይጀምራሉ። ዕጽዋትና አዝዕርት እንቡጦች ይፈነዳሉ። የመብረቅ ነጎድጓድ ተወግዶ የሰላምና የሲሳይ ዝናብ ይዘንባል።

እንስሳት የጠራ ውሃ እየጠጡ፣ ለምለም ሳር እየነቸረፉ ይቦርቃሉ። እርሻ የከረሙ በሬዎች፣ ጭነት የከረሙ አህዮች መስከረም አንጻራዊ የእፎይታ ወርኃቸው ነው። ነጎድጓድ በአዕዋፋት ዝማሬ ይተካል። ንቦች አበባ ይቀስማሉ፤ ቀፏቸውን ያደራሉ። ቢራቢሮ ሳትቀር ‘በመስከረም ብራ ከኔ በላይ ላሳር’ ብላ ትከንፋለች።

ለሰው ልጆች የመስከረም ደጅ ሲከፈት ግብዣው የትየለሌ ነው። ምድር ብቻ አይደለችም በ’እንቁጣጣሽ’ የምትዋበው። መስከረም ለሰው ልጆችም በተለይም ለወጣቶች የፍቅር፣ የእሸትና የአበባ ወር ነው። የሰላም፣ የንጹህ አየር፣ የጤና ድባብ ያረብብበታል። የጋመ በቆሎ እሸት ጥብስ፤ ቅቤ ልውስ፤ ቅቤ በረካ፤ መስቀል፣ ደመራ ይናፈቃል። የተጥፋፋ ይገናኛል። ‘ሰኔ መጣና ነጣጠለን’ ብለው ወርኃ ሰኔን የረገሙ ተማሪዎች ተናፋቂያቸውን ያገኛሉና ‘መስከረም ለምለም’ ብለው ያሞካሹታል። የገበሬው የሰብል ቡቃያ ያብባል፣ እሸት ያሽታል። ጉዝጓዝ ሣር፤ ትኩስ ቡና ይሸታል።

'መስከረም ሲጠባ ወደ አገሬ ልግባ …’ እንዲሉ የተሰደዱት በአዲስ ዓመት መባቻ የአገራቸውን አፈር ያማትራሉ። ’ኢዮሃ አበባዬ፤ መስከረም ጠባዬ’ የሚሉ ሕጻናት ተስፋና ምኞታቸውን በወረቀት ያቀልማሉ፤ የአበባ ስዕላት ይዘው በየደጃፉ ይሯሯጣሉ፣ የ’ዕደጉ’ ምርቃት ያገኛሉ፤ በደስታ ይንቦጫረቃሉ። በዚህ ድባብ ነው እንግዲ መስከረምን የግዑዛንም የሕይወታውያንም የነፃነት፣ የተስፋና የፍቅር ወርኅ ተደርጎ የሚናፈቀው።

በጥቅሉ የባለ13 ወር ፀጋዋ ኢትዮጵያ መስከረም ሁለንተናዊ ውበቱ ድንቅ ነው። ትዕምርቱም ጉልህ ነው። ለብዙ ሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ በስልጣኔ ወደኋላ እየተሳበች ወደ ድህነት ከርመት ከገባች ክፍለ ዘመናት ተቆጥሯል። ተፈጥራዊ አዱኛ ሳይርቃት በእርስ በርስ ጦርነት፣ በጠላት ፍላጻዎች ብዛት፣ በድንቁርና... የተነሳ ሰንኮፎቿ አልተነቀሉላትም። ዛሬም በብዙ ምስቅልቅሎሽ ውስጥ በመሆኗ ይህን ወርኅ መስከረም በሙሉ ሰላም ማክበር አልቻለችም።  

ደመራ  እና  መስቀል

የወራት ቁንጮው መስከረም ደማቅ መልኮች መካከል አንዱ ደመራ፤ በዓለ መስቀል ነው። የዕንቁጣጣሽ ተከታይ ብሔራዊ በዓል ነው -መስቀል። መስቀልና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ትስስራቸው ጥብቅ ነው። መስቀል ከመንፈሳዊ አንድምታው ባሻገር ባህላዊ ትውፊቱ በቀላሉ አይገለጽም። እንደ ኃይማኖተ አበው ሀተታ መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን፣ ለፍጡር የሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጸበት ዓርማ ነው። በዚህም መስቀልን አማኝ ምዕመናንና ካህናት የድህነትና የእምነት ምልክታቸው፤ የርኩስ መንፈስ ማባረሪያ መሳሪያቸው አድርገው ብቻ አይደለም የሚመለከቱት። ነገረ መስቀሉ እምነቱ፣ ባህሉ፣ ትውፊቱ ብዙ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን መስቀል ወራሪዎችን ድል የነሱበት፣ የጠላት ሴራ ያከሸፉበት፣ ጨለማን በብርሃን የለወጡበት የታሪካቸውና ባሕላቸው የተጋድሎ ምልክት አድርገው ይወስዱታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 10 ቀን ‘ተቀጸል ጽጌ’ በሚል የክርስቶት መስቀል ግማድ (ቀኝ እጁ ያረፈበት ክፋይ) ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ኢትዮጵያ የገባበትን ቀን ታከብረዋለች፤ መስከረም 17 ቀን ደግሞ መስቀሉ የተገኘበትን። መስከረም 17 ቀን የሚከበረው በዓለ መስቀል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባለፈ ባህላዊ ትውፊትነቱ የጎላ በመሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይናፈቃል።

የመስቀል ክብረ በዓል መለያው ደመራው ነው። የደመራ አደማመርና ማብራት ስነ ስርዓት በሁሉም የኢትዮጰያ አካባቢዎች ተመሳሳይ እንዳልሆነ ደራሲ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሄር ይተርካሉ። በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በዋግኸምራ፣ በአዊና በከፊል ጎጃም ደመራ ማታ ላይ ተደምሮ ንጋት ላይ ይለኮሳል። በከፊል ጎጃም፣ በሸዋ፣ በአዲስ አበባ፣ በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በወላይታና ሌሎች የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ እንደየ አካባቢው ተለምዶ መስከረም 16 ከዕኩለ ቀን ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ ደመራው ይለኮሳል።

መስቀል እንደየአካባቢውና ባህሉ የሚናፈቅበት ዕልፍ ገጽታዎች አሉት። ለምሳሌ በእኔ ገጠራማ ትውልድ ቀዬ በወፍ በረር ስገልጸው፤ በቅድመ ደመራ ሰሞን ተራራ ለተራራ፣ ወንዝ ለወንዝ፣ ቋጥኝ ለቋጥኝ በልጅነት ወኔና ስስት እንኳትናለን፤ የደመራ ግንድ፣ አደይ አበባ፣ የደቦት ደረቅ እንጨት ለመልቀም። መስከረም 16 አመሻሽ ከብቶች በጊዜ ከተሰበሰቡ፣ ወደ ግርግም ከገቡ፣ የመስከረም 16 መዓልት ለፅልመት ሲረታ የመንደሩ ወጣቶች ወደ ተለመደችዋ ‘አፋፍ’ እንሰባሰባለን-አፋፏ ለደመራ ትመረጣለችና። ከአጎራባች መንደሮች የተሻለ ደመራ ለመደመር እንጥራለን። እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት በጨለማ ደመራችንን ደምረን፣ የደመርነውን ደመራ እንቧለሌ ዞረን፣ ባርከንና መርቀን፣ ጨፍረን ወደየ ቤታችን እንበታተናለን፤ ከሰዓታት በኋላ ለመገናኘት ደግሞ እንነፋፈቃለን። የመስከረም 16 አዳር እንቅልፍ ይነሳል። በሌሊት ተነስቶ፣ ችቦ አብርቶ፣ ‘እዮሃ ደመራ’ እያሉ ወደ ደመራው ስፍራ ለመሄድ፣ ደርሶም ደመራውን ከሌሎች አጎራባች የመንደር ደመራዎች ቀድሞ ለመለኮስ ጉጉቱ የትየሌሌ ነው።

አጠባብ ላይ ከቤት ያለ ጉብል ሁሉ (ልጃገረዶችና ወንዶች) ወደ ደመራ ያመራሉ። ከምድጃ አልያም ከክብሪት እሳት ጭሮ ደቦቱን (ችቦውን) ይለኩሳል። ደቦቱ በእሳት ከተያያዘ በኋላ ወላጆቹን፣ ከብቶቹን፣ የጓሮ አትክልቱን፣ በደጃፍ ያሉ ሕይወታዊያንን በሙሉ “እንጎረጎባህ፤ እንጎረጎባችሁ” ይላል። ተጠያቂውም “ዓመት ዓመቱን ያድርስህ” ማለት ይጠበቅበታል። ለብሽሽቅ ከሆነ ደግሞ “ወስፋት ይላጥህ'” ማለቱ አይቀርም ይሄኔ በተቀጣጠለ ችቦ አጸፋውን የመስጠት ልምድ አለ። ከቤት ተነስተን ደመራው ከተደመረበት አፋፍ እስከምንደርስ በአንድ እጃችን መጠባበቂያ ደቦት፣ በሌላው ያቀጣጠልነውን ችቦ ይዘን የደመራ ግጥሞችን እየደረደርን እንቀጥላለን። የመስከረም እኩሌታ ውብ ማሳ ከየቤቱ ከሚወጡ የችቦ እሳት ነበልባል ብርሃን ይታጀባል። ከሚዘወተሩ ስንኞች መካከልም፡-

እዮሃ አበባዬ

መስከረም ጠባዬ…

እዮሃ አረሬ አረሬ

መስቀል ጠባ ዛሬ

በሸዋ በትግሬ… ይጠቀሳሉ።

ከደመራው ስፍራ ስንደርስ የ’እንጎረጎባህ! እንጎረጎባሽ! እንጎረጎባችሁ’ ድምጾች ይበረታሉ። ሁሉም ልጆች እስኪሰባሰቡ መልካምም ሆነ እኩይ የአጸፋ መልሶች እየተመለሱ ጥቂት ይቆያል። ደመራውን ሶስት ጊዜ ‘እዮሃ አበባዬ፣ መሰከረም ጠባዬ” እና ሌሎች የራስን ደመራ የሚያሞካሹ፣ የሌሎቹን የሚነቅፉ፣ ዘመኑ የጥጋብ ዘመን እንዲሆንና እንዲባረክ የሚመኙ ስንኞች እየተገጠሙ እንቧለሌ እንዞረዋለን። በስፍራው በዕደሜ ታላቅ የሆነ ሰው ለችቦ ማስገቢያ ክፍት በተተወው የደመራው ገጽ በኩል የተለኮሰ ደቦቱን ያስገባል። ሌላው ሁሉ እሱን ተከትሉ ወደ ደመራው ደቦቱን ይጨምራል። ደመራው መቀጣጠል ይጀምራል፣ ጭሱም ይጨሳል፣ የእሳቱ ነበልባል ከመስከረም የንጋት ውርጭና ብርድ ይገላግላል።

ደመራውን ዙሪያውን ተኮልኩለን ወሬ፣ ሀሜት፣ መበሻሸቅ፣ ባለፉት ክረምት ወራት ስለነበሩ የተሳታፊዎች ገጠመኞች በአያሌው እንሰልቃለን። የተጣላም ሳይቀር ታርቆ ያወራል፣ በዛ መበሻሸቅም አልፎ አልፎ የሚጣላ ቡጢ የሚሰናዘርም አይጠፋም። በዚህ መልክ የደመራው አምድ (ምሰሶ) እስክትወድቅ፣ ሌሊቱ የአህያ ሆድ እስኪመስል እናነጋለን። ምሰሶው ወደዬት እንደሚወደቅ ለማየት እንጓጓለን። ወደ ምሥራቅ ከወደቀ የጥጋብ ዓመት፤ ወደ ምዕራብ ከሆነ ግን የችጋር ዓመት ተደርጎ ይገመታል። ምሰሶው ከወደቀ በኋላ ሌላ ትዕይንት ይከተላል።

እንጨት ካለቀ በአካባቢው ከሚገኝ የግለሰብም ሆነ የወል ንብረት እንጨት በመስረቅ ከደመራው ላይ ይጨመራል። በቀያችን የመስቀል አንዱ ባህሉ የቦቆሎ እሸት ናፍቆት ነው። ቦቆሎ ቢያሽትም ባያሽትም፣ ከማሳው ተዘንጥፎ በይፋ በሰፈሩ የሚቀመሰው የመስቀል ዕለት ነው። እናም በሌሊት ተቧድነን በሚያመች ቦታና ማሳ በመግባት ቦቆሎ የመስረቅ ልማድ አለ። ባለቦቆሎውም ከነገ በኋላ ቢሰማም ዓመታዊ ደንብ ስለሆነ ቦቆሎ ማሳዬ ተጎዳብኝ ብሎ አይቆጣም። በደመራው ፍም ጠብሰን እሸቱን እንበላለን። ከደመራው ዓመድ በግንባራችን ላይ የመስቀል ምልክት እናደርጋለን። የዛሬ ዓመት አድርሰኝ ስለት እንሳላለን።

አሁን ሰማዩ የአህያ ሆድ መስሏል። ቀጣዩ ተግባራችን በደቦ ወደ መንደር መዞር ነው። ቀሪ ችቧችንን አቀጣጥለን እንደ ዕድር በአንድ ደመራ አባል በሆኑ ቤቶች ሁሉ እየዞርን ‘እንጎረጎባችሁ’ እንላለን። እንደ ከተማ ልጅ ሳንቲም አይደለም የሚሰጠው። ለዚያ ብለን ባዘጋጀናት ሳህን፣ ጣሳ ወይም ሌላ መያዣ ዱቄት እንለምናለን። የበሬና የላም ስም እየጠራን፤ እንገጥማለን። ሁሉን ቤተሰብ ካዳረስን በኋላ የሰበሰብነውን ዱቄት ‘ዓመት ዓመቱን ያድርሳችሁ’ ከሚል ምርቃት ጋር ተሸክመን ወደ ደመራው ስፍራ እንመለሳለን። ከዛው የደመራው ጉባኤ ወስኖ ለተመረጠች ሴት ዱቄቱ ይሰጣል። አነባበሮ እንድትጋግር በወጣቶች ዘንድ ቀጭን እመቤት (ባለሙያነቷ የተመሰከረላት) ይሰጣል። የማገዶ እንጨትም ተለቅሞ ይሰጣታል። ተመራጯ ሴት ባለትዳር ብትሆንም ባትሆንም ዳቦ ጋግራ ለአመሻሽ ለማድረስ አደራዋን ትረከባለች።

የመስቀል ዕለት በጎች ታርደው፣ ጠላ ቀርቦ፣ ሰፈርተኛው ተሰባስቦ ሲጫውት ይውላል። መስቀል የወል ክብረ በዓል ነው፤ የጋርዮሽ አከባብር። በተለይም ከሰዓት ለአንዳንድ ስራ ራቅ ካለ ቦታ የሄደ ሁሉ ይሰባሰባል። አመሻሽ ላይም እንደደመራው ምሽት ዕለት ሰው ይሰባሰባል። በዚህ ዕለት የግድ በጋራ በዓሉን ማክበር ስለሚያስፈልግ የተጣላ ጎረቤት ሁሉ ይታረቃል፤ ያለፈው የክረምት ጨለማ ጊዜያት ክፉ ደግ ጉዳዮች ይወራሉ። ልጆች ይቦርቃሉ። የጠዋት አደራ ተቀባይ ሴት የጋገረችውን አነባብሮ (መክፈልትም ይባላል) ታቀርባለች። እነዚህ ከመስቀል ጥቂት የአንድ ቀዬ ገጽታዎች መካከል ናቸው። እናም መስቀል ከእንቁጣጣሽ በበለጠ መልኩ በኛ መንደር ይናፈቃል። ሁሉም እንደየ አካባው ትውፊትና ወጉ ይህን ዓመታዊ ሁነት ይናፍቃል….

መስቀል በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ርዕሰ ዓውደ ዓመት ይመስላል። በደቡብ ኢትዮጵያ መስቀል ከኅይማኖታዊ ይዘቱ ባህላዊ ጎኑ ይጎላል። ጉራጌዎች፣ ጋሞዎችና ሌሎችም መስቀልን ከሁሉም በዓላት የበለጠ ይናፍቁታል። የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት የፍቅር፣ የደስታና የእርቅ በዓል ነው-መስቀል። በጋሞ ብሔረሰብ ባሕል በዋዜማው ሰው ቢሞት አንኳን በሌሊት ተወስዶ ይቀበራል እንጂ ለቅሶ እንደማይለቀስ ይነገራል፤ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም ልዩ መኖ እንደሚቀርብላቸው ይነገራል። ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው በጋሞዎች ደግሞ ‘ለመስቀል ያልሆነ ዱንጉዛ ይበጣጠስ’ በሚመሰል መልኩ የባህል ልብስ አለባበስ እንደሚዘወተር መምህር ካህሳይ (በህብረ ብዕር ድርሰታቸው) ጽፈዋል።

መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ አውራው በዓል ነው። ለቀጣዩ መስቀል ዝግጅት የሚጀመረው የአሁኑ ባለፈ ማግስት ነው። ሁሉም የየራሱን ዝግጅት ያደርጋል አባወራ ሰንጋ ለመግዛት፣ እማወራ ማጣፈጫውን ለማዘጋጀት፣ ወጣቶች ደመራና ደቦት ለማዘጋጀት፣ ልጆች ምርቃት ለመቀበል የየራሳቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። መስቀል ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ ለትዳር የደረሱ ሚስት የሚያጩበትና የሚመርጡበት ጥላቻና ቂም በፍቅርና በይቅርታ የሚታደስበት ነው። ይህም በመሆኑ በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል ትልቅ ቦታ የሚቸረው ዓውራ ብሔራዊ በዓል ነው።

ደመራ ዛሬ አመሻሽ ጀምሮ ይከበራል። ደመራ ‘ደመረ፣ ተሰባሰበ’ ከሚለው ስርዎ ቃል መጣ እንዲሉ ሊቃውንት በኃይማኖት አባቶች ይገልጻሉ። ደመራ በከተሞች ደማቅ ነው። በዓለ መስቀል ግን በአብዛኛው የጋርዮሽ ሳይሆን የተናጠል አከባብር ይስተዋልበታል። በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው መስቀል በአዲስ አበባ የደመራ በዓል በብሔራዊ ደረጃ በ’መስቀል አደባባይ’ ይከበራል። የመንግስትና ኃይማኖት ተቋማት መሪዎች፤ የውጭ አገር ጎብኝዎች ይደመሙበታል።

ጎረቤታሞች፣ የሩቅ የቅርብ ዘመዳሞች ተደምረው የጋራ ችቦ የሚለኩሱበት ዕለት ነው። ደመራና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋና፣ የተስፋ… እሴቶች የሚገለጹበት ባህላዊና ኃይማኖታዊ ከብረ በዓል ነው። አገሬው ያላባሩ ፖለቲካዊ ቁርሾዎች እና ያላባሩ ግጭቶች እንዲረግቡ፣ ቂምና ጥላቻ እንዲወገድ፣ ጆሮ ቸር ወሬ እንዲሰማ፣ የአንድነት ዘመን እንዲሆን ያለውን ብሩሕ ተስፋ በየዓመቱ ይመኛል፤ ዘንድሮም።

በኅይማኖታዊ አንድምታው አዳም ዕፀ በለስ በልቶ ሞትን አስከተለ። እየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ስለሰው ልጆች መስቀል ተሸክሞ ሞትን ገደለ። መስቀሉ የብሉይ ኪዳን ሙታን እና የአዲስ ኪዳን ሕያዋንን በፍስሃ ተነስተውበታል። ከቀራኒዮ ተራራ ጫፍ ላይ ክርስቶስን የሰቀሉበትን ሰባት ክንድ ቁመት ያለው መስቀል፤ ከስቅለት በኋላ አልባሌ ቦታ ላይ አርቀው ቆፍረው ቀብረውታል። ዳሩ ሰው ዕውነትን ምን ያህል በጥልቀት ምሶ ቢቀብረው፤ አንድ ቀን መውጣቱ አይቀርምና በደመራው ተገለጠ።

ኢትዮጵያም የገዛ ልጆቿ መውጋት ከጀመሯት ውለው አድርዋል። እናታቸውን መግረፍ ከጀመሩ ባጅተዋል። 'ያጠባ ጡቷን፣ ያጎረ እጇን' መንከስ ከጀመሩ ከራርመዋል። ሐቁን ሸሽገው ከል ካለበሷት ዓመታት ተቆጥረዋል።  ግን የኢትዮጵያ ዕውነቶች እንደተዳፈኑ አይቀሩም፤ ይገለጣሉ። እንደ ንግስት ኢሌኒ በፍቅር የተቃጠሉ ልጆቿ ደመራዋን ለኩሰው ሐቋን ተምሶ ከተቀበረበት ቁልቁለት ማውጣታቸው አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም