የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በሚያከናውናቸው ሥራዎች ውጤት እያስመዘገበ ነው–የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

377

ሐረር፤ መስከረም 16/2015 (ኢዜአ) የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በትራንስፖርት ፣ሎጀስቲክስና በአቅም ግንባታ እያከናወነ ባለው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር እና የኢትዮ- ጅቡቲ ስታንደርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘውን የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የአቅም ግንባታ የቴክኖሎጂ ስራዎችን  ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር  በትራንስፖርት፣በሎጀስቲክስና በአቅም ግንባታ እያከናወነ ባለው ሥራ  ውጤት እያስመዘገበ ነው።

በተለይ ባለፉት 6 ወራት  በኩባንያው የተከናወኑ ስራዎች አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና መሻሻል እየታየበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ ተቀዛቅዞ የነበረው መንገደኞችን የማጓጓዝ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው ፤ የቡና ንግድን ለማሳለጥ ቡናን  ሙሉ ለሙሉ  በባቡር ማጓጓዝ መቻሉን ተናግረዋል።

በሎጀስትክስ እንቅሰቃሴው ላይ አበረታች  ስራ መሰራቱn ገልጸው፤ በዚህም  ወደ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የሎጀስቲክ ወጪን መቀነስ የሚያስችል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ የባቡር መካኒካል፣ኤሌክትሪካል፣በአይሲቲና በፊዚካል ጥገና ስራዎች ላይ  ወጣቶችን በማሰልጠን የአቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በአቅም ግንባታ ሥራዎች አበረታች ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውንም አስታውቀዋል።

ለባቡር አገልግሎት ስኬታማነት  ኢትዮጵያና ጅቡቲ  በጋራ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ከኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት መሰራቱን አብራርተዋል።

የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ እሰኪያጅ ዶክተር አብዲ ዘነበ በበኩላቸው የባቡር ትራንስፖርቱ በተለይ በውጭ ንግዱ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸውን ምርቶች የማጓጓዝ ሥራ ማከናወኑን አስረድተዋል።

ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ 55 ሚሊየን ሊትር ዘይት በባቡር ትራንስፖርት ማጓጓዝ መቻሉን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ተቀብሎ ለባቡሩ በሚሰጠው የኤሌትሪክ ሃይል ሲስተም በሁለት ዙር ሰልጣኞችን በማስመረቅ ወደ ሥራ ማሰማራት መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የአቅም ግንባታ ዳይሬክተር ኢንጅነር ሳሙኤል ብሩ ናቸው።

 በአሁኑ ወቅት  በሶስተኛ ዙር ሰልጣኞችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።

በምህንድስናው ዘርፍ የመጀመሪያ ሰልጣኞች በድሬዳዋ  ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን በመግለጽ።

የአቅም ግንባታ ስራ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈ ቴክኖሎጂው በራስ አቅም እንዲሰራ እገዛ ለማድረግ እንደሚያግዝ ታናግረዋል።

የኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር  የሥራ አመራር  ቦርድ የባቡር ዘርፉ አቅም ግንባታ የደረሰበትን  ደረጃ በመሰክ ጉብኝት ተመልክተዋል።

በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙት ስራዎችን አስመልክቶም በድሬዳዋ ከተማ ምክክር አካሂደዋል።