ዩኒቨርሲቲው 13 አዳዲስ የትምህርት መረሃ ግብሮች ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው

158

ጎባ፤ መስከረም 16/2015 (ኢዜአ) መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ 13 አዳዲስ የትምህርት መረሃ ግብሮችን በመጀመሪያና ድህረ ምረቃ ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የፍላጎት ዳሰሳ ውጤትና በረቂቅ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄዷል።

በመድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር አዲሱ አሰፋ ተቋሙ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸውን 54 የተለያዩ የትምህርት መስኮች በድህረ ምረቃ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በስምንት የሁለተኛ ዲግሪና  አንድ የሶስተኛ ዲግሪ አዳዲስ የትምህርት መረሃ ግብሮች የድህረ ምረቃ ስልጠና ለመጀመር የአዋጭነት ዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ጤና፣ ምህንድስና፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንዲሁም የመሬትና የውሃ ሀብት አጠቃቀም ተቋሙ ከሚጀምራቸው የድህረ ምረቃ የትምህርት መረሃ ግብሮች ይገኙበታል።

በመጀመሪያ ዲግሪ አራት የተለያዩ መረሃ ግብሮችም እንዳሉም ተጠቁሟል።

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ  የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር በዛብህ ወንድሙ ናቸው።

“ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ መስክ የበቃ ዜጋ ለማፍራት ለሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል፡፡

በተለይም   በጤናው ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችለውን የአዋጭነት ዳሰሳ፣ የስርዓተ ትምህርት ቀረፃና ክለሳ እያደረገ  መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ዶክተር በዛብህ እንዳሉት ፤ በትምህርት ዓይነቶቹ ስልጠና ከመጀመሩ በፊት የአዋጭነት የዳሰሳ ጥናት በዩኒቨርሲቲውና በባለድርሻ አካላት ማስተቸት የተሻለ ግብዓት ከማስገኘቱም በላይ ለመርሀ ግበሩ  ውጤታማነትና ቀጣይነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ ውጤት መሰረት አዳዲስ ለመክፈት የቀረቡት የትምህርት ዓይነቶች አካባቢያዊና ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላና ተቋሙን አንድ እርምጃ ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተቀረፀው ስርዓተ ትምህርት በትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው  የውስጥና የውጭ አካላት ከተተቹ በኋላ ፀድቆ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከተሳተፉ ምሁራን መካከል ዶክተር ከድር አብዳ በሰጡት አስተያየት፤ በአንድ የትምህርት ዓይነት ስልጠና ከመጀመሩ በፊት በገበያ ላይ ያለው ፍላጎት በዘርፉ የሚመረቁ ተማሪዎችን ሊቀበል የሚችል ተቋምና ሀገራዊ ፋይዳቸው መታየት እንዳለበት ተናግረዋል ፡፡

መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  በድሀረ ምረቃ የስልጠና መረሃ ግብሮች ለመጀመር ያቀረባቸው የትምህርት ዓይነቶች የአካባቢውንና ሀገራዊ ፍላጎትንና ፋይዳን መሰረት ያደረጉና ወቅታዊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው ተሳታፊ ዶክተር ጄይላን ቃስም ፤ አዲስ ለሚጀመሩት የትምህርት መስኮች የአዋጭነት የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱ የማዳበሪያ ሀሳብ  ከማስገኘትም በላይ ለመርሀ ግብሮቹ  ውጤታማነትና ቀጣይነት ጉልህ ስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው ያመለከቱት፡፡

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት አዲስ የሚጀምሩትን  ሳይጨምር ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በ61 የትምህርት ዓይነቶች እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተቋሙን በመረጃ ምንጭነት ጠቅሶ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም