በክልሉ ለአርሶ አደሩ 20 ሺህ የሚጠጉ የሞተር የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ይሰራጫሉ---ዶክተር ይልቃል ከፋለ

175

ባህር ዳር (ኢዜአ) መስከረም 16/2015 "በአማራ ክልል የመስኖ ምርታማነትን ለማሳደግ 20ሺህ የሚጠጉ የሞተር የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ብር ወጭ የተደረገባቸውን 10ሺህ 467 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለአርሶ አደሮች እንዲከፋፈሉ ተድርጓል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፣ በበጋ ወቅት የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች ያለው መሬት ከመስኖ ልማት ውጭ እንዳይሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ትናንት ለአርሶአደሩ የተከፋፈሉትን ጨምሮ የክልሉ መንግስት 20ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖችን ለአርሶ አደሩ እንደሚያሰራጭ አመልክተዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት የክልሉ መንግስት አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ ሲያመርትበት ከነበረው የግብርና ሥራ ወጥቶ በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ እንዲያመርት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

ባለፈው ዓመት ከህልውና ዘመቻ ጎን ለጎን 40ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ማልማት መቻሉን አስታውሰው፣ ከእዚህ ልምድ በመውሰድ ዘንድሮ 250 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

"ለዚህም መንግስት የውሃ ፓምፖችን ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊ የሆነ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ለአመራሩ አቅጣጫ ወርዶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በልማቱ ውጤታማ ለመሆንም አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የሚደረግላቸውን ሙያዊ ድጋፎች ወደተግባር መቀየር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ ናቸው።

ይህን ያህል የመልማት አቅም ቢኖርም እየለማ ያለው መሬት ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰው፤ በመስኖ የማልማት አቅምን ለማሳደግ ተረባርቦ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ቢሮ ሀላፊው እንዳሉት የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የፋይናንስ ችግር ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

"መንግስት የአርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ ችግሩን ለመፍታት ባደረገው ጥረት በአሁኑ ወቅት ለውጥ እየታየ ነው" ብለዋል።

"የግብርና ሚኒስቴሩ አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው በአማራ ክልል በመስኖ የመልማት አቅምን ለማሳደግ በአመራሩ በየደረጃው እየተሰሩ ያሉ ተግብራት የሚያበረታቱ ናቸው" ብለዋል።

የመስኖ ልማቱን ለማሳደግ የፌዴራል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ "የግብርና ሚኒስቴርም ተጨማሪ 3 ሺህ 400 ፓምፖችን ለአርሶ አደሩ ያቀርባል" ብለዋል።

በመስኖ የማልማት ዕድል ቢኖርም በቴክኖሎጂ እጥረት ምክንያት በአቅማቸው ልክ ማምረት ሳይችሉ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሮቢት ባታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ዋለ ደመወዝ ናቸው።

መንግስት ለመስኖ ልማት የሚያስፈልገውን የውሃ መሳቢያ ፓምፕ በማቅረቡ አመስግነው፣ በቀጣይ  በልማት ሥራው ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በውሃ ፓምፕ የርክክብ መርሃ ግብር ላይ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስታዳዳሪዎችና አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም