በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ662 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል

113

መስከረም 16 ቀን 2015(ኢዜአ)በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ662 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብን የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን፣ ሀብትና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡
በዚህም በተጠናቀቀ የ2014 በጀት ዓመት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፤ ሶስተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ተከናውኗል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው የገቢ ማሰባሰብ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉ ነው የተጠቀሰው፡፡
የታላቁ ኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንዳሉት፤ በ2015 በጀት ዓመት ለግድቡ ግንበታ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ወራት ለግድቡ ግንባታ ከ662 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ያመላክታል ብለዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዚህ ደረጃ መድረስ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፤ ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቀሪዎቹ ጊዜያትም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 
የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በቴክኖሎጂ የታገዙ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም ጭምር ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡