በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረት የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመፍታት መልካም አጋጣሚ ነው

117

ባህርዳር መስከረም 16/2015 በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የተከሰተውን ቀውስ ለመቋቋም በኢትዮጵያ የተጀመሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረት መገጣጠም መልካም አጋጣሚ እንደሆነ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረ ስላሴ ገለጸ።

አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረ ስላሴ እንዳለው የአየር ንበረት ለውጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በማምረትና በመገጣጠም ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ለሚጥሩ አገራት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

የአየር ብክለት በዓለም ላይ አሁን የምናየውን ድርቅ፣ የሰደድ እሳት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በሽታና ሌሎች ችግሮችን በሰው ልጆች ላይ እልቂት እያስከተለ ይገኛል።

የነዳጅ ባለቤት የሆኑና በነዳጅ የሚሰራ መኪና አምራች አገራት ይሄን ችግር ወደ ጎን በመተው ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በማሰብ በሚፈጥሩት ጫና የዓለም አገራት ሌሎች አማራጮችን ከማየት ተገድበው ቆይተዋል።

አሁን ላይ ችግሩ ተባብሶ በራሳቸው ላይ ቀውስ በመፍጠሩ የበለጸጉ የአለም አገራት ጭምር ፊታቸውን ወደ ታዳሽ ሃይል ልማት ማተኮራቸውን ሻለቃ ሃይሌ አስረድቷል።

ኢትዮጵያም ያላትን የግድብ፣ የነፋስ፣ የጂኦተርማልና ሌሎች የታዳሽ ሃይል አቅሞችን በመጠቀም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተፈጠረውን አጋጣሚ መጠቀም አለባት ብሏል።

በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ መንግስት ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት ባሻገር ግለሰቦች ለነዳጅ የሚያወጡትን ከፍተኛ ገንዘብና በየማደያው የሚገጥማቸውን ሰልፍ የሚያስቀር ነው።

እንደ ሃይሌ ገለጻ የራሱ ድርጅት የሆነው ማራቶን ሞተርስ ይሄን ቀድሞ በመገንዘብ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ መኪና በመገጣጠም ምርቱን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስረድቷል።

በተጨማሪም የቻርጅ ማዕከላትን በማስፋፋት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች አስመጭዎችና የሚገጣጥሙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

"አሁን በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪን ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ የለም" የሚለው ሻለቃ ሃይሌ መንግስት ከታክስ ነጻና ዝቅተኛ ቀረጥ የማበረታቻ ስርዓት መዘርጋቱ ለዘርፉ ማደግ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ የሚስተዋለውን የመብራት መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አሳስቧል።

ዘርፉን ለማልማት የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱ ፋና ወጊ ተግባር ያደርገዋል ያለው ሻለቃ ሃይሌ ለሌሎች ዩንቨርስቲዎች አርአያ የሆነ ተግባር ነው ብሏል።

የባህርዳር ዩንቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከአገር ውስጥና ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአገራችን እድገት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አሁን ላይ ያስጀመረው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ ዘርፍ የሰው ሃይል በጥራትና በብቃት ለማፍራት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪን በአገራችን ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ወርክ ሾፕ በባህርዳር ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት ትናንት መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም