የጤና አገልግሎትንና የባለሙያዎችን የስራ ሁኔታ ለማሻሻል እየተሰራ ነው - ሚኒስቴሩ

107

ሀዋሳ መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ከሰው ሃይል ልማት ጎን ለጎን የጤና አገልግሎትንና የባለሙያዎችን የስራ ሁኔታ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ17ኛ ጊዜ በተለያዩ የህክምና ሙያ ያሰለጠናቸውን 421 ተማሪዎች ዛሬ  አስመርቋል።

በምርቃቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንዳሉት ካለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ወዲህ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የባለሙያ እጥረት ለመፍታት ከዩኒቨርስቲዎችና   ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በዚህ የጋራ ጥረት የጤናና ህክምና ትምህርት የሚሰጡ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ ሀገር ከ37 በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ይህም የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ይረዳን ዘንድ የህክምና ዶክተሮችን፣ ነርሶችን፣ ሚድዋይ ፈሪ እና ጤና መኮንኖች  ጥምርታን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

ከሰው ሃይል ልማት ጎን ለጎን አሁን ላይ እንደ ጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት እና የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ሁኔታ ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የጤና ፖሊሲ ክለሳ፣ የአምስት ዓመት የጤና ዘርፍ የለውጥ እቅድ በመንደፍና የሀገሪቱ ጤና አገልግሎት የሚመራበትና የሚገዛበት አዋጅ ዝግጅትና የትመህርት ጥራት እንዲሻሻል የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን  ሚኒስትር ዴኤታው ለአብነት አውሰተዋል።

እነዚህ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከርና ፍሬያማ ለማድረግ አዲስ ተመራቂዎች የሙያ ሥነ ምግባር በመላበስ ማህበረሰባቸውን በተነሳሽነትና በርህራሄ ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር አየለ አሳስበዋል።  

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው 321 አካዳሚክ ፕሮግራሞችን በመክፈት  የህክምና ስፔሻሊትንና ሰብ ስፔሻሊትን ጨምሮ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ከ32 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ከማፍራት በተጓዳኝ መጠነ ሰፊ የምርምር ስራዎችንና ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያቀርበውን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ የመጣ ተቋም መሆኑንም አመላክተዋል።

የሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ኡርጌሳ ዋርሳሞ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ኮሌጁ በዛሬው እለት ለ17ኛ ዙር በተለያዩ ጤና ሳይንስ ሙያዎች 264 የቅድመ ምረቃ እና ለ13ኛ ዙር ደግሞ 157 የህክምና ዶክተሮችን አስመርቋል።

ከነዚህም በተጨማሪ ለድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት 11  በሜዲካል ራዲዮሎጂ ድህረ ምረቃ መርሃ ግብር በማሰልጠን ማስመረቁን አመላክተዋል።

ከተመራቂ ሀኪሞች መካከል ከታናሽ እህቱ ጋር የተመረቀው ዶክተር አስተዋይ አሹሮ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ከእህቱ ጋር በመመረቁ ድርብ ደስታ እንደተሰማው ገልፆ በቀጣይ በስራ አለም ቆይታው የሙያው ስነምግባር እና በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ሁሉንም ወገኑን በእኩልነት ለማገልገል ተዘጓጀቷል።

የዶክተር አስተዋይ እህት የሆነችው  የእለቱ ተመራቂ ዶክተር  ኤልሮኢ አሹሮ  በበኩሏ ከአንድ ቤት ሁለት ሰው በህክምና ዶክተሬት ሲመረቅ ልዩ ደስታ እንዳለው ትገልጻለች።

ጠንክረው በመማር በተሻለ ውጤት መመረቃቸውን ጠቅሳ “የህክምና ሙያ ደግሞ ዘር ሃይማኖት ቋንቋ እና ሌሎችም ነገሮች ሳይገድቡት ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠትን የግድ ስለሚል ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅነቷን አረጋግጣለች።

ለሙያዋ እና ለህብረተሰቡ ታማኝ በመሆንም በስራ ዘመኗ የሚጠበቅባትን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጓንም ተናግራለች።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የዪኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም