በመዲናዋ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ የልማታዊ ስራዎች ይቀጥላሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

239

መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) በመዲናዋ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ የልማታዊ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በእሳት አደጋ ምክንያት ቤታቸው ተቃጥሎባቸው የነበሩ አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታው መጠናቀቁን ተከትሎ ከንቲባዋ በዛሬው እለት አስረክበዋል።

በእሳት አደጋው ተቃጥለው የነበሩት 9 መኖሪያ ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት ከኤምሲጂ ኮንስትራክሽን ጋር በመተባበር ቤቶቹ በአዲስ መልክ ተገንብተው በመጠናቀቃቸው ባለቤቶቹ ተረክበዋለ።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት በመዲናዋ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እውን የሚያደርጉ የልማታዊ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራአስፈጻሚ  ዶክተር ብሩክ ከድር፤ በእሳት አዳጋ ሳቢያ ቤታቸው የተቃጠለባቸውን ወገኖች በአጭር ጊዜ በመገንባት ማስረከብ መቻሉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ደቦ ቱንካ በበኩላቸው ከትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጎን ለጎን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤት ግንባታ የተከናወነላቸው ነዋሪዎች በተደረገላቸው በጎ ተግባር በማመስን  መተባበርና መተጋገዝ ካለ መፈታት የማይችል ችግር አለመኖሩን በተግባር ተመልክተናል ብለዋል።