በቡራዩ ከተማ በተፈጠረው ግጭትና መፈናቀል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሁለት አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

795

አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 በቡራዩ ከተማ በተፈጠረው ግጭትና መፈናቀል ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሁለት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገለጸ።

ከዚህም በተጨማሪ ለዚህ ህገ ወጥ ተግባር የተያዘ የጦር መሳሪያም 4 ክላሽንኮቭ ጠመንጃና 12 ሽጉጥ መድረሱን የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደረጀ ባይሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የተጠርጣሪዎች ቁጥር  እየጨመረ ነው ያሉት ኮማንደሩ እስካሁን 364 መድረሳቸውንም አብራርተዋለው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሁለት ሰዎች፣ አንድ የፖሊስ አባልና አንድ የጸጥታ ኃላፊ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ብለዋል።

ማንኛውም ሰው ኃላፊም ሆነ ሌላ ሰው ከህግ አግባብ ውጪ ሆኖ ከተገኘ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል ነው ያሉት የፖሊስ አዛዡ።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ የሚደረገው ዝግጅትም መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቄቸው ለመመለስ  ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ቄሮዎች ጋር በመሆን ለመመለስ ዝግጅት ጨርሰናል ብለዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ንብረት ለማስመለስም  ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማዋ የፀጥታ ሁኔታም አሁን ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል ብለዋል።