የአንድነት፣ የሠላም እና የአብሮነት ማብሰሪያ የሆነው የወላይታ ብሄር የዘመን መለወጫ የ"ጊፋታ" በዓል በወላይታ ሶዶ በድምቀት እየተከበረ ነው

210

ሶዶ መስከረም 15/2015 (ኢዜአ) የአንድነትና የሠላም እንዲሁም የአብሮነት ማብሰሪያ በዓል የሆነው የወላይታ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው የ"ጊፋታ" በዓል በወላይታ ሶዶ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

በብሄሩ ዘንድ ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲሱ መሸጋገሪያ ብስራት ተደርጎ የሚቆጠረው የጊፋታ በዓል የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ ላይ በርካታ ቁጥር ያላው ህዝብ የተገኘ ሲሆን ለበዓሉ ድምቀት የሆኑ በባህላዊ አልባሳት ደምቀው በጋራ እያከበሩት ይገኛል፡፡

በዓሉ ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገሪያ፣ የአንድነትና ሠላም እንዲሁም የአብሮነት ማብሰሪያ ተደርጎም በብሄሩ ተወላጆች ዘንድ ይታመናል፡፡

በመሆኑም በአሮጌው ዘመን የተፈጠሩ ቁርሾና ቂም ልባዊ በሆነ ዕርቅና ወንድማማችነት በማደስ የሚቀበሉት በዓል በመሆኑ የይቅርታና የሰላም በዓል በመባም ይታወቃል፡፡

በድምቀት እየተከበረ ባለው በዓል ላይ የፌዴራል ፖሊስ የኦርኬስትራ ማርሽ ባንድ በከተማው ልዩ ጣዕመ ዜማ እያሰማ ይገኛል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የፎቶ ኤግዚቢሽን የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ለእይታ ቀርበዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ሚኒስተሮች፣ በሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች፣ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተወከሉ እና በርካታ ቁጥር ያላቸው የአከባቢው ማህበረሰብ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም