ኢትዮጵያ የተናጥል ጣልቃ ገብነትና በኃይል ፍላጎትን የመጫን ሙከራ አትቀበልም -አቶ ደመቀ መኮንን

243

መስከረም 14 / 2015(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የተናጥል ጣልቃ ገብነትና ጫና ማሳደር የሚፈልጉ አካላትን እንደማትቀበል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ሰብአዊ መብትን ለፖለቲካ መሳሪያነት መጠቀም ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።

77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ ኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ዛሬ ማምሻውን ንግግር አድርገዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓለም በአሁኑ ሰአት እየተፈነችባቸው ያሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት በትብብር መስራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ፣ማህበራዊ መስኮች ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገልጸዋል።

አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያን ልማት ለማደናቀፍ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ከሁለት ዓመት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ጥቃት መፈጸሙን አመልክተዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት አሳዛኝና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ከውጪ ኃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን የማፍረስ አላማ በሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልም ሆኖ ቀርቷል ነው ያሉት አቶ ደመቀ።

መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በሰላም እንዲፈታ እየሰራ እንደሚገኝና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሂደቱን ሊደግፍና ሊያከብር ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የተናጥል ጣልቃ ገብነትና በኃይል ፍላጎትን የመጫን ሙከራ እንደማትቀበልና እንደዚህ አይነት አካሄዶች ፍሬ አልባ እንደሆኑ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ እንደሚያገኙ በጽኑ ታምናለች ያሉት አቶ ደመቀ ዓለም ይህን የአፍሪካ ፍላጎት በማክበር ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል።

የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ሉዓላዊነት ማክበር፣ነጻነት፣ጣልቃ አለመግባትና የጋራ መከባበር የሚሉትን የባለብዙ መድረክ ግንኙነት መርሖዎች ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መርሕን እንደምታከብርና ከታችኛው ተፋሰስ አገራትም በፍትሐዊነት ተጠቃሚነት የውሃ ሀብቷን ታለማለች ብለዋል።ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የጋራ ተጠቃሚነትን ባከበረ መልኩ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ አመልክተዋል።

አቶ ደመቀ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እውቅና እንዲሰጥና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።