ለአገርና ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራት ይቻላል-ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

62
አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 የተለያዩ የፖለቲካ አቋም እያራመዱ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ መሆኑን የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞኪራሲያዊ ድርጅት/ኦህዴድ ለዚህ የሚረዱ ፈር ቀዳጅ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ይገልጻሉ። የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ ይህንን የተናገሩት ኦህዴድ በጂማ እያደረገ ባለው ዘጠነኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ላይ በታዛቢነት በተሳተፉ ጊዜ ነው። በጉባኤው ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል። በጉባኤው ላይ ኢዜአ አግኝቶ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ "አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ስለመከፈቱ ማሳያ ብቻ ሳይሆን  ጅማሮው የዴሞክራሲ ምህዳሩን የሚያሰፋ እንደሆነም ገልጸዋል። ብርጋዴር ጄነራል ኃይሉ ጎንፋ፤ የተባበረው ኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በሐሳብ ይሁን በኃይል ሲፈላለጉ የነበሩት አንድ መድረክ ላይ ሆነው ስለ ጋራ ጉዳይ መነጋገራቸው መቀጠል እንዳለበትና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት መጀመሩን የሚያሳይ ይመስለኛል  ብለዋል ። ኦህዴድ የተለያየ አመለካከት ያላቸውን አንድ ላይ አቅርቦ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረጉ  አንዱ የለውጥ መንገድ ና የህዝቡ የትግል ውጤት ነው ብዬ አስባለሁ ብለዋል ብርጋዴር ጄነራል ኃይሉ ጎንፋ ። በአንድ ላይ ሆኖ እንዲህ አይነት አገራዊ ራዕይ ያላቸው ከዚህ በፊት ሲገፉ የነበሩ ዛሬ መጥተው በአንድ መድረክ ላይ ሲገናኙ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ብዬ አስባለሁ ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ነፃነትና አንድነት ግንባር ሊቀመንበር ኮለኔል አበበ ገረሱ ናቸው  ። የኦሮሞ ዴሞከራሲያዊ ግንባር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዲማ ነጎ በበኩላቸው በኦህዴድ የ መደበኛ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ  በእንግድነት ተገኝተን ለጉባኤው መልእክት እንድናስተላልፍ እድል አግኝተን በየጊዜው በአገራችን ባለው ሁኔታ ምን መደረግ እንዳለበት  ለመጠቆም ሞክረናል ብለዋል በአገሪቱ ጥሩ አዝማሚያ እየታየ እንደሆነና ውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ገብተው እንድሰሩ ተደርጓል።በአገር ውስጥም ያሉት ከፖለቲካ ተጽእኖ ተላቀው በነጻነት ሊንቀሳቀሱና ሊደራጁ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል። ለወደፊቱም ሂደቱን በማስቀጠል በአገሪቱ እውነተኛ ፓርቲዎች እንደሚፈጠሩም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የፖለቲካ አቋም ብናራምድም የጋራ በሚያደርገን የህዝብና የአገር ጥቅም ማስከበር ላይ በጋራ መስራት እንደምንችል አመላካች ነው። እነሱም የበኩላቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት በማውሳት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም