ኬንያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ ናት-ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

82

መስከረም 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኬንያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ከአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃገራቸው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከጎረቤት ሃገራት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡

ኬንያ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ መሪዎች ጋር በጋራ ለመስራት በቀጠናው ያለውን ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እሳቸውን መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በቀጣናው ምንም ዓይነት አሉታዊ እንቅስቃሴ እንዲጎለብት እንደማይፈልጉ የገለጹት ፕሬዝዳንት ሩቶ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን በዚሁ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መመደባቸውም ከዚሁ በመነጨ ሃሳብ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶች ለችግሮቹ መፍትሄ እንደማይሆኑ መረዳት ያስፈልጋል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ሃገር የማስተዳደር ጉዳይ ማንም ሰው እንደሚያስበው ቀላል አለመሆኑ ሊዘነጋ አይገባም” ብለዋል፡፡

የሰሜን የኢትዮጵያን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካስፈለገ ትልቁን ሚና የሚወጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመሆናቸው ድጋፍና ትብብር ሊደረግላቸው እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል።

በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን የኬኒያ ራስምታት ሆኖ መዝለቁን ያልሸሸጉት ፕሬዝደንቱ ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸው የፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ አስተዳደር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሃገራቸው በሶማሊያ ጠንካራ መንግስት ባለመኖሩ በአልሸባብ ምክንያት ከባድ መስዋእትነት እየከፈለች መቆየቷን ገልጸው፤ይሄንን ለመከላከል አሁን ላይ በሶማሊያ ከፍተኛ ወታደራዊ ሃይል መሰማራቱን ጠቅሰዋል።

የኬንያ ወቅታዊ የቤት ስራም በሶማሊያ የተረጋጋ መንግስት በመፍጠር ሽብርተኝነትን መከላከልና በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም