ባህላዊ እሴቶችን ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየተሰራነው - ቢሮው

130

ሆሳዕና: መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) ለአንድነትና ሰላም ግንባታ ሚና ያላቸው የብሄረሰቦች ቱባ እሴቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የሀድያ ብሄር ባህል፣ቋንቋና ታሪክ ሲምፖዚየም ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በክልሉ የሚገኙ ለአንድነትና ለሰላም ዓይነተኛ ሚና ያላቸው የብሄረሰብ በዓላት እንዲተዋወቁ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓላቱ ለሰላም ለአብሮነትና አንድነት ማጠናከሪያና ማሳሪያ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

"በተለይም ሰርቶ መበልጸግ መከባበር ግብረገብነት ትጋትና ተስፋን የሚያጭሩ እንዲሁም ስንፍናና ያለመስራትን የሚኮንኑ በመሆናቸው ሀገራችን ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ በዓላቱን አውጥቶ መጠቀም ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው" ብለዋል።

በፖለቲካው ረገድ ሰላማዊ ትግልና የሀሳብ ልዕልናን የሚያበረታቱ መሆናቸውን አንስተው ይህ በኢትዮጵያ የኖረ የቀደምት የዘመናዊነት ምንጭ መሆናችንን አንዱ ማሳያ መሆኑን አቶ ሀይለማሪያም ተናግረዋል።

በተለይም ሀገር ሊያሻግር የሚችል ምክንያታዊና ተፅእኖ ፈጣሪ ዜጎች እንዲፈጠር እንዴ ያሆዴ ያሉ  ሀገር በቀል የሆኑ ባህላዊ እሴቶች ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ጥረቶች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ባህሎቹ ይዘታቸውን ጠብቀው ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ ሰንዶ ከማስቀመጥ ጀምሮ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች በማካሄድ የማስተዋወቁ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው:-የሀድያ ብሄር ለሀገር ሰላምና ህልውና ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዋጻ ያደረጉ የበርካታ እሴቶች ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳደር የህዝቡን እሴቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል  ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

"የሀድያ ብሄር የዘመን መለወጫ የሆነዉ ያሆዴ በዓል ምግብና መጠጥ በጋራ ተሰባስቦ በመብላትና በመጠጣት በደስታ የሚከበር በዓል ነው" ያሉት ደግሞ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እርስቱ ናቸው።

ከበዓሉ ክዋኔዎች በዋናነት ቂምና ቁርሾን አስወግዶ እርቅ በማውረድ አዲሱን ዓመት መቀበል መሆኑን ጠቅሰው "ይህም ልዩነትን በማጥበብ በዜጎች መካከል አንድነትና ሰላም እንዲጠናከር ያደርጋል" ብለዋል

በዚህም በሀዲያ ዘንድ ያሆዴ የሰላም ተምሳሌት በዓል ተደርጎ እንደሚቆጠር ገልጸዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የያሆዴን የቀደምት ዕሴት የሚያሳዩ ጥናቶች በምሁራን የቀረቡ ሲሆን ዕሴቱ ነባር ይዘቱን ይዞ እንዲቀጥል ጥረት መደረግ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል ።

በስነ ስርአቱ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማሀበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶከተር ዲላሞ ኦቶሮ በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የፖለቲካና ርዕዮተ አለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደ ሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም