ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

95

ደሴ መስከረም 13/2015 ( ኢዜአ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ቤተሰብ ተማሪዎች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አወል ሰይድ በተደረገ የድጋፍ ርክክብ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት  በመተጋገዝ፣ በመረዳዳትና በአብሮነት ይህን አስቸጋሪ ወቅት ማለፍ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

"ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ህወሓት ውድመት ቢደርስበትም  መልሶ እየተቋቋመ የመማር ማስተማር ሂደቱንና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን ዳግም አጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል ፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቤተሰብ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከድጋፉ መካከል 40 ሺህ ደብተርና 3ሺህ 800 እስክርቢቶዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ "ድጋፉ ለደቡብ ወሎ፤ ሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች፣ ለደሴ ከተማ አስተዳደር፣ ለደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች የሚሆን ነው" ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ አማረ በበኩላቸው አንድም ሕጻን በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታው እንዳይቀር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ድጋፍ አቅም ለሌላቸው ወገኖች እፎይታ ከመስጠቱ ባሻገር ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

"ወሎ ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው ህወሓት የደረሰበትን ከባድ ውድመት ተቋቁሞ ዛሬ የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ቤተሰብ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለአካባቢው ህዝብ ያለውን አጋርነት በተግባር ያረጋገጠ ነው" ያሉት ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተወካይ ዶክተር መልሰው ተፈራ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ተወካይ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው "ዛሬ የተደረገው ድጋፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና ዘማች ቤተሰብ ተማሪዎች እንዲውል ይደረጋል" ብለዋል።

"ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል"ሲሉም አክለዋል ።

በድጋፍ ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና የየዞኖች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም