በጎንደር ከተማ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች በድጋፍ ተበርክተዋል- መምሪያው

59

ጎንደር መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰብ ተማሪዎች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች በድጋፍ መበርከታቸውን የከተማው ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በከተማው የነገ ተስፋ የተቀናጀ የልማት በጎ አድራጊ ድርጅት 1 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች ዛሬ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ ነጻነት መንግስቴ እንደተናገሩት ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ሰፊ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው፡፡

ከመስከረም ወር 2015 መጀመሪያ  ጀምሮ በተካሄደ የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ ንቅናቄ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው  የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በማስተባበር በተደረገ ሃብት ማሰባሰብ  ትምህርታቸውን ለመከታታል ለተመዘገቡ ከ8ሺ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶቹ በድጋፍ መሰራጨታቸውን አመልክተዋል፡፡

“ድጋፉ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ከትምህርት ገበታ እንደይለዩ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና የክፍል ውስጥ መድገምን ለመቀነስ ያግዛል”ብለዋል።

በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በተካሄደ የአዲስና ነባር ተማሪዎች የምዝገባ ስራ ከ114ሺ በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ ከ91ሺ በላይ ተማሪዎች ተመዘግበው ትምህርት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

”በእውቀትና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ትምህርት ቤቶችን በግብአት ማጠናከር ተማሪዎችን ደግሞ መደገፍ ይገባል” ያሉት ደግሞ የነገ ተስፋ የተቀናጀ የልማት በጎ አድራጊ ድርጅት የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ደምሴ ናቸው፡፡

ድርጅቱ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት መማር ላልቻሉ ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመው  በዛሬው እለትም በከተማው በ17 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 1ሺ 800 ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱ በጎንደርና በደባርቅ ከተሞች በሚገኙ ሶስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 530 ለሚደርሱ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በማዘጋጀት የቁርስና የምሳ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ድርጅቱ ባለፉት ሶስት አመታት ከ12ሺ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ደብተርና እስክሪቢቶ እንዲሁም የመጻህፍትና ደብተር መያዣ ጨምሮ  ቦርሳዎችን በማቅረብ  3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው  ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በከተማው የአዘዞ ተክለሃይማኖት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አቤል መልካሙ በበኩሉ ”ቤተሰቦቼ ጡረተኞች በመሆናቸው ለእኔ ደብተር ገዝተው ለማስተማር ተቸግረው ነበር” ብሏል፡፡

የተደረገልኝ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ትምህርት እንዳላቋርጥና በትምህርቴም ደካማ እንዳልሆን የሞራል እገዛ ያደርግልኛል” ሲል ምስጋና አቅርቧል፡፡