የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ከ43 ሺህ ለሚበልጡ ኢንተር ፕራይዞች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ነው

396

ባህርዳር መስከረም 13/2014 (ኢዜአ)የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ43 ሺህ ለሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ቢሮው  ከክልሉ ለተውጣጡ ወደ 1ሺህ ለሚጠጉ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት  በ2014 ዓ.ም ዕቅድ አፈፃፀምና በ2015 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ  ላለፉት አራት ቀናት በባህርዳር ሲያካሂድ የሰነበተውን ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው ኢንተርፕራይዞች የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው በሀገር ውስጥና በውጭ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየሰራ ነው።

ለኢንተርፕራይዞቹ የሀገር ውስጥ ገበያ ትስስር የሚፈጠረው ለግንባታ የሚውሉ የጠጠርና ብሎኬት ምርቶች፣ በኮብልስቶን፣ በማዕድን፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ ባልትናና ሌሎች ምርቶች መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በውጭ ሀገር የገበያ  120 ኢንተርፕራይዞች የአሳ ምርት፣ የእንጨትና እንጨት ምርት ውጤቶች በማስተሳሰር ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ።

ዕቅዱን ለማሳካት በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ኢንተርፕራይዞቹ ጥራቱን የጠበቀ ምርት አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢንተርፕራይዞቹ የሚመረተው ምርት የት አካባቢ የተሻለ ገበያ ሊያገኝ እንደሚችል በመለየት የማስተሳሰሩ ስራ ትኩረት እንደተሰጠውም አቶ አወቀ አስረድተዋል።  

የምስራቅ ጎጃም ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀሐይ ቦጋለ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዞቹ የሚያጋጥማቸውን የገበያ ችግር ማቃለል የምንችለው የገበያ ትስስር በመፍጠር ነው ብለዋል።

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ለ3 ሺህ 220 ኢንተርፕራይዞች የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር  እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በድጋፍና ክትትል ስራው ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በማስተካከል ኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸው ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የንግድ ትርኢትና ባዛር በማዘጋጀት ከባለሃብቶች ጋር የማስተሳሰር ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸውን ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አቅርበው በመሸጥ እንዲጠቀሙ ከኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለኢንተርፕራይዞቹ ተከታታይ ድጋፍ በማድረግም የግብርና፣ ማኒፋክቸሪንግ፣ የማዕድንና ሌሎች ምርቶችን በጥራት አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙላት መኮንን በበኩላቸው ኮንስትራክሽን፣ በማኒፋክቸሪንግ፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ በ7 ሺህ ኢንተርፕራይዞች ለሚደራጁ 141ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተቀምጦ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።        

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ31 ሺህ ለሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር በሀገር ውስጥ ገበያ መፍጠሩ መቻሉን ከክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም