የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ የውሃ ሀብት ጥበቃ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው -ሚኒስቴሩ

87

ባህርዳር መስከረም 13/2015 “በገጠርና በከተማ የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ የውሃ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር አስታወቀ ።

ሚንስቴሩ ከተጠሪ ተቋማትና ከሁሉም ክልሎች የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ጋር በ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ የሶስት ቀን የውይይት መድረክ በባህርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

የውሃና ኢነርጂ  ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ  እንደገለጹት የውሃ ሃብት መገኛ አካባቢዎችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ለአገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት የማዋል ስራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ በተያዘው 2015 በጀት ዓመት 6 ሚሊየን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“በተጨማሪም በሶላር፣ በባዮ ጋዝና ሌሎች አማራጭ የሃይል ምንጮችና ከአገራዊ ግሪድ ከሚገኘው የግድቦች ሃይል ከከተማ እስከ ገጠር በፍትሃዊነት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በሀገሪቱ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኢነርጂ አቅርቦትን ለማስፋት ለገጽና ከርሰ ምድር የውሃ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተለይም እንደ እንቦጭ ያሉ መጤ አረሞች ወንዞችን፣ ሃይቆችንና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት በጋራ ለማስወገድ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ  አስገንዝበዋል።

ሚንስትሩ አክለው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመተግበር የውሃ አካባቢዎችን የማመንጨት አቅም ለማሳደግ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጅነር ሙሃመድዝያድ ገለቶ በበኩላቸው በክልሉ በድርቅ ምክንያት በየጊዜው የሚጎዱ ዞኖችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የውሃ አቅርቦት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በያዝነው 2015 በጀት ዓመት 2 ሚሊየን የሚሆን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ 8ሺህ 800 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

በኢነርጂው ዘርፍም የጸሃይ ሃይልን በመጠቀምና በባዮ ጋዝ የገጠሩን ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

“በተያዘው 2015 በበጀት ዓመት በመንግስት፣ በረጅ ድርጅቶችና በህብረተሰቡ ትብብር የንጹህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ተቋማት ግንባታ ስራዎች ይካሄዳሉ” ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማእድን ልማት  ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጅነር ፍጹም መኩሪያ ናቸው።

ከንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ 303 ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 600 የንጹህ መጠጥ ውሃና 35 የመስኖ ፕሮጀክቶችን በአዲስ መልክ በማስጀመር ግንባታቸውን በማፋጠን ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በአገሪቱ 62 ነጥብ 4 በመቶ ላይ የሚገኘውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን በያዝነው 2015  በጀት ዓመት መጨረሻ 69 በመቶ ለማድረስ ግብ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ከውሃና ኢነርጂ  ሚኒስትር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።