የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

መስከረም 13/2015(ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት ዓመት ከ5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስታውቀዋል።

በፓን አፍሪካን መንፈስ የአህጉሪቱ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ እድገት እንዲያስመዘግብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ መስፍን ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው አንድ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ተጽዕኖዎችን  ወደ እድል በመቀየር ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

የበረራ ኢንዱስትሪው በኮቪድ-19 ተፅዕኖ ስር በወደቀበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ መከላከያ ጭምብል፣ መመርመሪያ ኪት፣ ክትባት እና ሌሎች አስፈላጊ መሳሪያዎችን በማጓጓዝ የተሻለ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ባከናወነው ውጤታማ ተግባር መንገደኞችን በማጓጓዝ ይገኝ የነበረውን ገቢ በጭነት አገልግሎት ማካካስ እንደቻለ በማንሳት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎቱን በማሳደግና ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም አየር መንገዱ በሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ከ66 በላይ የበረራ መዳረሻዎች ላይ አገልገሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ እድገት እንዳላስመዘገበ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት አፍሪካዊያን 80 ከመቶ የሚሆነውን የበረራ አገልግሎት የሚያገኙት ከአፍሪካ ውጭ በሆኑ አየር መንገዶች መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህን ለመቀየር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳሚ አየር መንገድነቱን በማስቀጠል የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ እድገት እንዲያስመዘግብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን የበለጠ በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቷን እንድታፋጥን ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቶጎው ስካይ፣ የማላዊ፣ የዛምቢያ፣ የኮንጎ እና የናይጄሪያ አየር መንገዶች ስኬት እንዲያስመዘግቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አቬየሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተመራጭና ግንባር ቀደም የበረራ አገልግሎት በመስጠት የተለያዩ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን ማግኘት ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም