ህዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል-የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

273

ሐዋሳ፣ መስከረም 13/2015 (ኢዜአ)፡ በክልሉ ህዝባዊ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ በክልሉ የሚከበሩ ህዝባዊ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር እንዲቻል የጸጥታ መዋቅሩ  አሳታፊና የተቀናጀ የጸጥታ ዕቅድ ማዘጋጀቱን  አስታውቀዋል።

የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ ያሆዴ፣የወላይታ ጊፋታ፣የጋሞ ዮ መስቃላና ሌሎችም በአደባባይ የሚከበሩ የብሔረሰቦችና የደመራ መስቀል በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር  በሰላም  እንዲከበሩ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በዓላቶቹ በየአካባቢው በድምቀት የሚከበሩ መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዓላቱ ካላቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንጻር ፍጹም ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ የክልሉ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል።

የክልሉ ፖሊስ በየመዋቀሩ ከሚገኙ የጸጥታ አካላትና የጸጥታ ስራውን የሚያግዙ ማህበረሰብ አቀፍ  አደረጃጀቶች ጋር በተቀናጀ መልኩ ሰላምን የማስከበር ስራ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ስጋት የሚሆኑ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጸጥታ ኃይል ፈጥኖ በማሳወቅ ለሰላም  ማስጠበቅ ስራ ሲያደርገው የቆየውን  አጋርነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

''ሠላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው'' ያሉት ኮሚሽነር አለማየሁ፤ በየአከባቢው የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በተቀናጀ መንገድ ሰላምን በማስጠበቅ የውስጥ ሰላምን ለማወክ የተለያየ ተልዕኮ ይዘው  ለሚንቀሳቀሱ አካላት ዕድል ባለመስጠት ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ  ገልጸዋል ።

ኮሚሽነር  አለማየሁ ለሀገር ሉዓላዊነትና ህልውና መከበር  በተለያየ ግንባር  በግዳጅ ላይ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም