በስኳር ፋብሪካዎች ከሸንኮራ አገዳ በተጨማሪ በ850 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች እየተመረቱ ነው

202

መስከረም 13 / 2015 (ኢዜአ) በስኳር ፋብሪካዎች ከሸንኮራ አገዳ በተጨማሪ በ850 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎች እየተመረቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አስታወቀ።

የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባና የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራሮች በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ከሸንኮራ አገዳ በተጨማሪ በተለያየ ስብል የተሸፈነውን ማሳ ጎብኝተዋል።

ከዚህ ቀደም በስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ምርት የተመረተበት ማሳ መልሶ ጥቅም ላይ ለመዋል ለአንድ ዓመት ያለ አገልግሎት ይቀመጥ ነበር።

ለአብነትም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ በየዓመቱ ከ800 እስከ 1000 ሄከታር መሬት ጦም ያድር እንደነበር ነው የተነገረው።

መንግስት ማንኛውም ማሳ ጦም ማደር የለበትም በሚል የጀመረውን ንቅናቄ ተከትሎ ሳይታረስ ይከርም የነበረውን መሬት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን የአፈር ማገገም ስራ መጀመሩ ተነግሯል።

በዚህም ፋብሪካዎች ከስኳር ምርት በተጓዳኝ መሬቱን በስንዴ፣ ማሾ፣ ቦለቄ፣ ሩዝ፣ ቦቆሎና ሌሎች ሰብሎች እየሸፈኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባ ተናግረዋል።

አቶ ወዮ እንዳሉት በክረምት ዝናብ ወንጂ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ስኳር ፋብሪካዎች ከ850 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለምቷል።

በሰብል ከተሸፈነው መሬትም ከ33 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

በፋብሪካዎቹ ካለው የመሬት ስፋትና ኃብት አንጻር የተሰራው ስራ አነስተኛ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የበለጠ መሰራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህም ፋብሪካዎች ከስኳር ምርት በተጨማሪ ከተለያዩ ሰብሎች ምርት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያግዛቸዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በበጋ መስኖ የተለያዩ ሰብሎች የማልማቱ ስራ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በዚህም ከስኳር ልማቱ በተጨማሪ በፋብሪካዎቹ በተለይ እንደ አገር በተያዘው ስንዴን በመስኖ የማልማቱ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይ በኦሞ ስኳር ፋብሪካ፣ በወንጂ፣ በተንዳሆ ስንዴን በመስኖ የማምረት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ያለውን አቅም ሁሉ በመጠቀም በበጋ ወቅት ቢያንስ በስምንት ፋብሪካዎች ላይ ምንም ዓይነት መሬት ጦም እንዳያድር መሬት ይሰራል ብለዋል።

ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ለምርጥ ዘር የሚውልን ጨምሮ 350 ሄክታር ስንዴ፣128 ሄክታር ቦለቄ፣30 ሄክታር የማሾ ሰብሎች መዘራታቸውን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አማን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ምርቶች ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት መታቀዱን ገልፀዋል።

በፋብሪካው ለዘር የሚሆኑ የተለያየ ዝርያ ያለው የስንዴ እና የቦለቄ ምርት እየተባዛ ይገኛል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛህኝ ናቸው።

በዚህም በስንዴ ብቻ ለ20 ሄክታር ያህል የሚበቃ የምርጥ ዘር እየተባዛ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከሌሎች ፋብሪካዎች ጋር በመሆን የዘር ብዜት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።