ጦርነቱን አሸባሪው ህወሃት እንደጀመረው እጁን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጠ የሽብር ቡድኑ ጋዜጠኛ አጋለጠ

288

መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ) ጦርነቱን አሸባሪው ህወሃት እንደጀመረው እጁን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጠ የሽብር ቡድኑ ጋዜጠኛ ፍጹም ጸጋዬ አጋለጠ፡፡የትግራይ እናቶች ህፃናት ልጆቻቸውን ከአሸባሪው ህወሃት አደን የሚደብቁበት አጥተው እየተነጠቁ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ሀገር የማስተዳደር ዕድል አግኝቶ በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያልፈጸመው ግፍ የለም፡፡

በአሸባሪው ህወሃት የስልጣን ዘመን የሰው ልጅ በህይወት እያለ ከጅብ ጋር ታስሯል፤ እጅና እግሩን ታስሮ ለዓመታት ጨለማ ቤት እንዲኖር ተደርጓል፤ የሰው ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ በፕላስቲክ እየተቃጠለ አካሉ እንዲጎድል መደረጉም እንዲሁ፡፡

አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን ከተወገደ በኋላም በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የክህደት ጥቃት ከመፈጸም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር በአገር ህልውና ላይ አደጋ የደቀነ ወረራ ፈጽሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ "እታገልለታለሁ" የሚለውን የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳያገኝ በመከልከል፣ ህፃናትን ወደ ጦርነት በመማገድ ለህዝቡ ደንታ የሌለው የጨካኞች ስብስብ መሆኑን አሳይቷል።

እጁን ለመከላከያ ሰራዊት የሰጠው የሽብር ቡድኑ ጋዜጠኛ ፍጹም ጸጋዬ ለኢዜአ እንዳለው፤ አሸባሪው ህወሓት የትግራይን እናቶች እያስለቀሰ አረጋዊያንን ያለ ጧሪና ቀባሪ እያስቀራቸው ነው፡፡

ጦርነትና ግጭትን የህልውናው ማራዘሚያ ያደረገው የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሶስተኛ ዙር ወረራ በመጀመር የሰላም ጸር መሆኑን አስመስክሯል ብሏል፡፡

የትግራይ ህዝብ ጦርነት ይብቃ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ይፈቱ እያለ ቢወተውትም በቆቦ በኩል ዳግም ጦርነት በመክፈት የትግራይ እናቶችን እረፍት ነስቷቸዋል ብሏል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል አልበቃ ብሎት ጦርነቱን በቆቦ በኩል ራሱ ጀምሮ የትግራይን ህዝብ መንግስት ጦርነት ከፈተብኝ በማለት እያታለለ መሆኑን ገልጿል፡፡

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ የትግራይ ህዝብ በሽብር ቡድኑ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ መደናገር የለበትም ነው ያለው፡፡

በዚህም በትግራይ እናት ልጇን ከአሸባሪው ደብቃ ማስቀረት አትችልም፤ ምክንያቱም ሁሉም ቦታ በሽብር ቡድኑ ኔትወርክ የተሳሰረ በመሆኑ ከዕይታቸው ማምለጥ አይቻልምና ይላል።

በትግራይ ክልል ፈልጎ ለውጊያ የሚሰለፍ ወጣት የለም የሚለው ጋዜጠኛ ፍጹም፤ ከሽብር ቡድኑ ኔትወርክ ለማምለጥ ዞንና ቀበሌ ቀይረው የሚሄዱ ህፃናትና ወጣቶችን ባሉበት ታድነው ታስረው ወደ ጦርነት እንደሚገቡ ገልጿል፡፡

በዚህም የትግራይ እናቶች ህፃናት ልጆቻቸውን ከአሸባሪው ህወሃት አደን የሚደብቁበት አጥተው እየተነጠቁ ለጦርነት እየተማገዱባቸው መሆኑን ተናግሯል።

"የትግራይ ህጻናትና ወጣቶች እየታደኑ ወደ ውጊያ እንዲገቡ ይገደዳሉ፤ ወደ ኋላ እንዳይመለሱም አሸባሪ ቡድኑ ገዳይ ስኳዶችን አዘጋጅቶ በጥይት ይጨፈጭፋቸዋል'' ሲልም ነው የተናገረው፡፡

የሚዋጉት ከፊትና ከኋላቸው በጥይት ተከበው ሞትን ብቸኛ አማራጫቸው አድርገው መሆኑን ገልፆ "ወደ ኋላ ሸሽታችኋል" በሚል በህወሓት አመራሮች የሚገደሉ ወጣቶችን በአይኔ አይቻለሁ ብሏል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ ሚያደርሰው በደል ያሰለቻቸው ወጣቶች "ዓላማ ለሌለው ጦርነት አንዋጋም" በማለታቸው የሽብር ቡድኑ ሰራዊት ተበትኖ እንደነበር ገልጾ፤ በክልሉ በዘረጉት ኔትወርክ አማካኝነት አስገድደው ወደ ውጊያ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል፤ እስካሁን የታሰሩ ወጣቶችም አሉ ብሏል፡፡

የትግራይ ህዝብ አሸባሪው በሃይል አፍኖ ይዞት በችግር ላይ ይገኛል የሚለው ጋዜጠኛው፤ ህዝቡ ሃሳቡን እንዳይገልፅ፣ ብሶቱን እንዳያሰማ በጭንቅ ውስጥ ይገኛል ብሏል።

አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ ከረሃብ አልታደገውም፤ ከመሞት አላዳነውም፤ አንዳች ጠብ የሚል ነገር አላደረገም ብሏል፡፡

በትግራይ ክልል ሚዲያዎች የሚነገረውና መሬት ላይ ያለው ሀቅ ፍፁም የተለያየ መሆኑን ገልጾ፤ የትግራይ ህዝብ ከዚህ ከባሰ ስቃይ ስለማይደርስበት ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ ከሽብር ቡድኑ አፈና መውጣት አለበት ብሏል፡፡

በትግራይ በርካታ ወጣቶች በአሸባሪው ህወሓት አመራሮች ከጦርነት "ሸሽታችኋል" በሚል ከኋላ መጨፍጨፋቸውንም ጋዜጠኛው ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም