"ያሆዴ" ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ አንድነትን ያጎለብታል--የዞኑ አስተዳዳሪ

134

ሆሳዕና መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነውን ”ያሆዴ” ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ለሀገራዊ አንድነት አስተዋጽኦ የጎላ ነው ሲሉ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብርሀም መጫ የብሔሩን የዘመን መለወጫ በዓል “ያሆዴ”ን ለማስጀመርና ባህላዊ እሴቱን ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ትናንት ማምሻውን መርቀው ከፍተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት “ያሆዴ” ባህላዊ ስርዓቱንና ወጉን ጠብቆ ማስቀጠል የሀድያ ብሔሩ ሁሉም ተወላጆች ሀላፊነት ነው።

በዓሉ ከሌሎች ጋር በአብሮነት፣ በመተጋገዝ፣ በመረዳዳት፣ በአንድነትና በይቅርታ የሚከበር በመሆኑ በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

ያለፈውን ዓመት ችግርና መከራ በመጣል ወደአዲስ ምዕራፍ የመሸጋገሪያ በዓል መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪ አመልክተዋል።

"ያሆዴ ጥላቻን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት የማይሸጋገሩበት እንዲሁም እርቀ ሰላም የሚወርድበት በዓል ነው” ያሉት አቶ አብርሀም፣ በዓሉ ሲከበር ደጋፊ የሌላቸውና አቅም የሌላቸውን በመደገፍ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነውን “ያሆዴ”ን ባህላዊ እሴቶች ይዘት አስጠብቆ በማስቀጠል ለትውልድ ማስተላለፍ ለሀገራዊ አንድነት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የሀድያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ርስቱ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ የሀድያ ብሔር የምግብ አዘገጃጀት፣ አለባበስና ባህላዊ ቁሳቁስን ጨምሮ ሌሎች ኩነቶችን ለአዲሱ ትውልድ በአግባቡ የማሳወቅ ዓላማ አለው ብለዋል።

"በባህልና በፎቶ አውደ ርዕዩ የብሔሩ ተወላጆች ቀደም ሲል ለበዓላት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሶችን ማየት ችያለሁ" ያለችው ደግሞ ከዞኑ ሌሞ ወረዳ ፎንቆ ከተማ የመጣችው ወጣት ማዕድያ አለሙ ናት።

የብሔሩ መለያ የሆኑ ነባር ታሪኮች እንዳይጠፉና ይዘታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የዞኑ አመራሮችና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም