የፌዴራልና የደቡብ ክልል የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በሶዶ ወረዳ እየለማ ያለውን የመኸር ሰብል እየጎበኙ ነው

131

ቡኢ፣ መስከረም 13 / 2015 (ኢዜአ) የፌዴራልና የደቡብ ክልል የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ እየለማ ያለውን መኸር ሰብል እየጎበኙ ነው።

የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጉብኝታቸውን እያካሄዱ የሚገኙት በሶዶ ወረዳ ሶሎቄ ቀበሌ ከ500 ሄክታር በላይ ማሳ ላይ በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን የስንዴ ማሳ ነው።

የወረዳው ምክትል ዋና አስተዳዳሪና ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብርሃኑ በቴ በሶዶ ወረዳ ከ35 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሁሉም ሰብሎች እየለማ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።

May be an image of nature, tree and grass

ጤፍ፣ ስንዴ፣ ቦቆሎና ሌሎች ሰብሎች እየለሙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ 75 በመቶ የሚሆነው ሰብል በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ እየለማ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ከአጠቃላይ እየለማ ካለው የመኸር ሰብል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

እንዲሁም የግብርና ሚኒስቴር ተወካዮች፣የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማልና ሌሎችም የሥራ ሃላፊዎች በጉብኝቱ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም