ኢትዮ ቴሌኮም ለፈጣን የመረጃ ልውውጥ የጀመረው ፍትሃዊ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ተደራሽነት ተጠናክሮ ቀጥሏል

99

ነገሌ፣ መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮ ቴሌኮም ለፈጣን የመረጃ ልውውጥ የጀመረው ፍትሃዊ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ተደራሽነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ፡፡

ድርጅቱ በደቡብ ሪጅን አራት ዋና ዋና ከተሞች በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አዲሱን ስርዓተ ትምህርት የሚያግዙ ዲጂታል ቤተመጻህፍትን ከፍቷል፡፡

በድርጅቱ ለነገሌ ከተማና አከባቢው የተከፈተው ዘመናዊ ዲጂታል ቤተ መጻህፍት ትናንት በከተማው አስተዳደር ከንቲባ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ሪጅን ቀጥተኛ ያልሆነ ቻናል ማናጀር በትእዛዙ አበራ ከድርጅቱ ማህበራዊ ሀላፊነቶች መካከል አንዱ የትምህርት ስራን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ጥራት ባለው ትምህርት ትውልዱን በእውቀት ለማበልጸግ ቤተመጻህፍቱ የተከፈቱት በነገሌ፣ ዲላ፣ ሀዋሳና ሻሸመኔ ከተሞች እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

አዲስ ለተከፈቱት የዲጂታል ቤተመጻህፍቱ በሙሉ ከክፍያ ነጻ የሆነ 11 ሜጋ ባይትስ ፈጣን የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት መልቀቁንም አስታውቀዋል፡፡

ለአዳዲሶቹ ቤተመጻህፍት በድርጅቱ የተለያዩ ሶፍት ዌሮችና መተግበሪያዎች 84 ወንበርና ጠረጴዛ፣ 4 ዘመናዊ ማተሚያ ማሽኖችና 84 ኮምፒውተሮች የተሟላላቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ቤተመጻህፍቱ በየቀኑ ከ8 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን በድርጅቱ ባለሙያዎች ጥገና ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸውም አብራርተዋል፡፡

ድርጅቱ በተጨማሪም በደቡብና በደቡብ ኦሮሚያ ከ10 የሚበልጡ ከተሞችን ፈጣን የ4 ጂ ተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ተደራሽ አድርጓል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በደቡብ ሪጅን ወላጆቻቸው በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ 2 ሺህ 690 ተማሪዎች 32 ሺህ 280 ደብተር ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ቤተመጻህፍቱን መርቀው የከፈቱት የነገሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሌ ሆሮ ለድርጅቱ ፍትሃዊ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅርቦቱ አዲሱ ስርአተ ትምህርት በጥራትና በፍጥነት እንዲተገበር ከማገዝ ሌላ ኢትዮ ቴሌኮም ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ የተግባር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ግሩም ዘነበ የድርጅቱ ድጋፍ አዲስ ባይሆንም የቴክኖሎጂ ተደራሽነቱ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል ቤተመጻህፍት ተደራሽነት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተማሪዎችን ሁለንተናዊ እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ ሌላ የመማር ማስተማሩን ስራ የሚያቀልና የሚያዘምን እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም