ለለውጥ ምዕራፎች ስኬት ተመራቂዎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል- አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ

283

መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተዳረጉ ላሉ የለውጥ ምዕራፎች ስኬት ተመራቂዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ አስገነዘቡ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስክ ያስተማራቸውን ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ለተመራቂ ተማሪዎች መዕልክት ያስተላለፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥና የህዝብ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ ለተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ስኬት መረባረብ ይገባል።

የተማረው የሰው ሃይል አቅሙንና ዕውቀቱን ማበርከት እንደሚገባ ገልጸው፤ ”የዛሬ ተመራቂዎች በተማሩበት የሙያ መስክ የሀገራችን ብልጽግና ለማረጋገጥ ብሎም ለመጪው ትውልድ መሠረት ለመጣል ባለራዕይ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።

ምሩቃኑ ያስተማረች ሀገር የምትጠብቀውን አበርክቶ መወጣት የሚያስችል ግብን መሰረት ያደረገ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝዋል፡፡

”የተጀመረው የለውጥ ምዕራፍ ከስኬት የሚደርሰው ሁሉም ዜጋ በየተሰማራበት መስክ የበኩሉን መወጣት ሲችል ነው” ብለዋል፡፡

ራዕይን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ስነ-ምግባር መኖር እንዳለበት አመልክተው፤ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚያስችልና አልሸነፍ ባይ ስነልቦና መያዝ ተገቢ መሆኑን አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል።

ምሩቃን የስራ ትጋት፣ ተስፋ ያለመቁረጥና ቁርጠኝነት በመላበስ ለዓላማቸው ሊኖሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ልዩነትን በማስወገድና እጅ ለእጅ በመያያዝ ሀገራዊ ለውጡን በስኬት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲም በዕውቀትና በምርምር የበቁ ዜጎች ለማፍራት ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በህክምናና ጤና ሳይንስ፣ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ እንዲሁም በግብርናና ምህንድስና ዘርፎች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 1 ሺህ 200 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ማስመረቁን ገልጸዋል፡፡

የሀገርን የዕድገት ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰው ሃይል ለማፍራት ዩኒቨረሲቲው በየጊዜ አቅሙን እያሳደገ እንደሚገኝም ዶክተር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ባለፈው ዓመት በ853 ርዕሶች ችግር ፈቺ ምርምር ማከናወኑን አመልክተው፤ ከተጠናቀቁ 182 ምርምሮች ውስጥ 25 ቱን ወደ ፕሮጀክት በመቀየር ለማህበረሰብ አገልግሎት ለማዋል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከተመራቂዎች መካከል በህምናና ጤና ሳይንስ የመዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ሙባረክ ንጉሥ ”ለዓላማዬ ተገዥ በመሆን ጠንክሬ በመስራተ ውጤታማ መሆን ችያለሁ” ብሏል።ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የዛሬን ጨምሮ ባለፉት 35 ዓመታት 73 ሺህ 824 ባለሙያዎችን ማስመረቅ መቻሉን ከዩኒቨረሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።