በሶማሌ ክልል የተጀመረው የስንዴ ልማት ሰብሉን ወደ ውጭ ለመላክ የታቀደውን ሀገራዊ ጥረት ለማሳካት ያግዛል- ክልሉ

102

ጅግጅጋ መስከረም 12/2815(ኢዜአ) ፡- በክልሉ የተጀመረው የስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ሰብሉን ወደ ውጭ ለመላክ የታቀደውን ሀገራዊ ጥረት ለማሳካት እንደሚያግዝ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኢብራሂም ዑስማን ተናገሩ ።

አቶ  ኢብራሂም ፤ በክልሉ ፋፈም ዞን በሚገኙ አዎባሬ እና ቱሊ ጉሌት ወረዳዎች  የለማ የስንዴና የበቆሎ   አዝመራ ከክልሉ አመራሮች ጋር ተዘዋውረው  ተመልክተዋል።  

የመስክ ምልከታው ዓላማ አርሶና  አርብቶ አደሮችን ለማበረታታት እና   ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ከወዲሁ መፍትሔ በመስጠት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲያግዝ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

በክልሉ በጠቅላላው 846 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 28ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል።

ለግብርና ልማት የሚውል  ከ10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በክልሉ እንዳለ ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ127 ሺ ሄክታር ማሳ ላይ ከለማው  ስንዴ  ብቻ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

በተለይ ክልሉ ያልተነካ ለም መሬት፣ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝ እና ከፍተኛ የከርስ ምድር ውሃ ባለቤት መሆኑን ማዕከል ያደረገ እና በጥናት የተደገፈ ሰፊ የመስኖ ስራ መጀመሩን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።

ይህም በተደጋጋሚ በክልሉ የሚከሰትን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ከመፍታት ባሻገር በመስኖ የሚመረተው  ወደ ውጭ የሚላክ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በክልሉ በሲቲ ዞን በመስኖ የተጀመረው የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ወደ ጅቡቲ  መላክ መጀመሩን በአብነት የሚጠቀስ እና ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል

የሶማሌ ክልል  ለስንዴ ልማት ብቻ  ያለው ምቹ  ስነ ምህዳር    ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ከፍተኛ በመሆኑ  ስንዴን በመጠንም በጥራትም ለማምርት የተጀመረውን ሀገራዊ ግብን  ለማሳካት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀው፤  ይህም ስንዴን ከውጭ የማስገባቱን ሂደት ለማስቀረት እና ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥራት ለማሳካት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

በመስክ መልከታው ላይ የተሳተፉት የክልሉ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት  ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልቃድር ኢማን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የግብርና ምርት እና ምርታማነት የማሳደግ ተግባራት በቴክኖሎጂ በመታገዝ በክልሉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች እያመረቱ የሚገኙት የስንዴ እና የበቆሎ ሰብሎች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ስንዴን በሀገር ምርት ራስን ለመቻል የሚከናወኑ ስራዎች ለማሳካት ያግዛል ሲሉ አስታውቀዋል።

በስንዴ ማምረት ከተሰማሩት የአዎባሬ ወረዳ አርሶአደሮች   ሙሴ አቴያ እንደተናገሩት ፤ በአካባቢየቸው  ተጠናክሮ የቀጠለው የስንዴ እና የበቆሎ ማምረት ስራ   የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

የቀጠለው የግብርና ልማት ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ ለአርሶአደሩ የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት ሆነው ማገዝ ፣ምርጥ ዘሮችን በፍጥነት ማቅረብ እና ለፀረ ሰብል ተዋህስያን መድሐኒት ማቅረብ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም