የመጪው በጋ ወቅት ዝናብ ከሚጠበቀው በታች ስለሚሆን የዝናብና የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ ማልማትና መጠቀም ይገባል-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

150

አዳማ፣ መስከረም 12 ቀን 2015(ኢዜአ) የመጪው በጋ ወቅት ዝናብ ከሚጠበቀው በታች ስለሚሆን የዝናብና የከርሰ ምድር ውሃን ማልማትና መጠቀም እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ እንደገለጹት ሊከሰት የሚችለውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ።

የመጪው በጋ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ በተደረገበት ወቅት በሀገሪቷ ደቡብና ምስራቅ ክፍል በሚያጋጥም የበጋ ዝናብ እጥረት ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ትንበያ መኖሩን ያነሱት ሚኒስትሩ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥራቱን የጠበቀ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ በሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ አውንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ምስራቅ ኢትዮጵያ የበጋ ዝናብ ከመደበኛ በታች መሆኑ የህዳር፣ ታህሳስና ጥር ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የዝናብ እጥረት የሚፈጠርበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካላት የአየር ሁኔታ ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃውን ወስደው ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቆላማው የሀገሪቷ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ያለፉት የአየር ሁኔታ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ወስደን ተግባራዊ በማድረጋችን ድርቁ ሊያስከትል የነበረውን የከፋ ጉዳት ተቋቁመናል ነው ያሉት።

በዚህም በእንስሳት ሀብቱ ላይ ጉዳት ቢደርስም የሰው ህይወት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ማድረግ ችለናል ብለዋል።

ባለፈው ክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የአየር ሁኔታውን በመከተል የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በተለይ በከተሞች የውሃ ማውረጃ ቦዮች ፅዳትና በግብርና ዘርፍ ተገቢው ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ግድቦች በቂ ውሃ እንዲይዙ በመደረጉ በበጋ ወቅት ሊኖር የሚችለውን የውሃ እጥረት መሸፈን እንደሚቻል የገለፁት ደግሞ የሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ናቸው።

በተለይ ደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች ቦረና፣ ጉጂና ባሌ፣ ሶማሊና ደቡብ ብሔር ብሐረሰቦች ክልሎች የበጋ ዝናብ ስርጭቱ ከመደበኛ በታች መሆኑን ጠቅሰው አርብቶ አደሩ በቀጣዩ ጥቅምት ወር ላይ የሚገኘው ዝናብ በመጠቀም ከወዲሁ መዝራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል መኸር አምራች በሆኑ የሀገሪቷ ክፍሎች የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም