የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች የሙያ ማህበር ዛሬ ተመሰረተ

147

አዳማ፤ መስከረም 12 / 2015(ኢዜአ) አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በመንግሥት የሚወጡ ፖሊስዎችና ስትራቴጂዎች በሚፈለገው መልኩ እንዲተገበሩ የሚዲያ ዘርፍ የሙያ ማህበራት ሚና የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ገለፀ ።

የኢትዮጵያ  አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች የሙያ ማህበር ዛሬ በአዳማ ተመሰረቷል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ወይንሸት ሙሉ ሰው እንዳሉት የማህበሩ መመስረት በዘርፉ ያሉ ጋዜጠኞች የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም በተሻለ እንድያስጠብቁ ያግዛል።

ከምስረታ ባለፈም ዘርፉን በተመለከተ የሚወጡ የህግ ማዕቀፎች በተጨባጭ ተግባራዊ ተደርገው የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ መስራት አለባችሁ ብለዋል።

አካል ጉዳተኞችን ያቀፈ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፖሊስዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች አካታች በሆነ መልኩ እንዲተገበር ሙያዊ ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባቸውም አክለዋል።

አዲስ የተመሰረተው ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረማርያም በበኩሏ ማህበሩ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞችን በሙያቸው በማሰባሰብ የተሻለ ስራ ለመስራት ያለመ ነው ብላለች።

በተለይም የአካል ጉዳተኛ ዜጎች መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ጭምር ትልቅ ዓላማ የሰነቀ መሆኑን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ የጋዜጠኞች የሙያ ማህበር መመስረቱ የሪፎርሙ አንዱ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቷ ተመዝግበው ከሚገኙት 4ሺህ 200 ማህበራት ውስጥ 2 ሺህ 200 የሚሆኑት ከለውጡ ወዲህ የተመሰረቱ የሲቪል ማህበራት መሆናቸውን ገልጸው ለውጡ አካታች የሆነ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት እውን እንዲሆን ለማስቻል ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ማህበሩ ሙያና ሙያተኞችን በማገናኘት የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም እንዲከበር ሲንቀሳቀስ ኤጄንሲው ተገቢውን ዕገዛ ያደርጋል ነው ያሉት ።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ዘርፍ ኮሚሽነር ወይዘሮ እርግበ ተክለሐዋሪያት እንደገለፁት ኮሚሽኑ ከአካል ጉዳተኞች የሙያ ማህበራት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ በአቅም ግንባታና ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ማህበሩ የሚሰራቸውን ስራዎች ኮሚሽኑ እያገዘ መሆኑን ገልፀው የአካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች የሙያ ማህበር መመስረቱ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ኮሚሽኑ ለሚሰራው ስራ ተጨማሪ አቅም የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም