የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ተምሳሌት ነው " በሚል መሪ ቃል መስከረም 21 እና 22 ይከበራል

315

መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል " ኢሬቻ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት ነው " በሚል መሪ ቃል መስከረም 21 እና 22 በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ ሃርሰዴ እንደሚከበር የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ  በሰጡት መግለጫ፤ በዓሉ መስከረም 21 ቀን2015 በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 22 ቀን ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሃርሰዴ እንደሚከበር ገልጸዋል።

ኢሬቻ የአንድነት፣የፍቅር፣የይቅር ባይነትና የመተባበር በዓል መሆኑን ገልጸው ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልዱ እንዲተላለፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ የኢሬቻን  እሴት በሚያዳብር መልኩ በዓሉን በአብሮነት ማክበር እንዳለበትም አመላክተዋል።

በዓሉ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ኃላፊው ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር በቱሪዝም ልማት የኢኮኖሚ አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢሬቻ በዓል የሰላም ተምሣሌት በመሆኑ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሁሉም የጋራ ሃላፊነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያውያንን ወንድማማችነት፣ አንድነት እና ፍቅር አጉልቶ የሚያሳይ በመሆኑ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በእለቱ ተገኝተው እንዲያከብሩትም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢሬቻ በዓል የቱሪዝም መስህብነቱ እንዲጎላ ለክብረ በዓሉ የሚመጡ ሰዎች የባህል አልባሳት እና መዋቢያ ጌጦችን በመልበስ እንዲያደምቁትም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም