የሳተላይት ምስሎች ጥራት ባለው መልኩ መረጃ ለሚሹ ተቋማት ተደራሽ እየተደረገ ነው- የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት

307

መስከረም 12 /2015 (ኢዜአ) የሳተላይት ምስሎች ጥራት ባለው መልኩ ወደ መረጃነት ተቀይረው መረጃ ለሚሹ የተለያዩ ተቋማት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ከሳተላይት ጥራት ያለው መረጃ መቀበል የሚያስችል የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያም ወደ ስራ መግባቱ ታውቋል።

በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት የሳተላይት ልማትና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር መላኩ ሙካ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በኢትዮጵያ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስኬታማ ስራዎች እየተከወኑ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ የላቀ እመርታ በማሳየት ላይ መሆኗን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር መላኳን አስታውሰዋል።

በጠፈር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሳተላይቶች ከመሬት በ628 ኪሎ ሜትር ረቀት ላይ በመሆን 13 ነጥብ 75 ሰፓሺያል ሪዞሊሽን የምስል ጥራት ያለው ምስል በመላክ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶቹ የሚላኩት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችም መረጃ ለሚሹ ሁሉ በግብአትነት እየዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሳተላይት ምስል መረጃ ፈልገው ለሚመጡ የተለያዩ ተቋማት ኢንስቲትዩቱ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከሳተላይት ጥራት ያለው መረጃ መቀበል የሚያስችል የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ በቅርቡ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልፀዋል፡፡

ከሳተላይት መረጃን የመቀበል ስራው ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሬት ላይ ሆኖ ከተለያዩ ሳተላይቶች መረጃ መቀበያ ጣቢያው አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያው አምስት እና ከዚያ በላይ ከሆኑ የተለያዩ አይነት ሳተላይቶች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ተቀብሎ በከፍተኛ ጥራት ማስተናገድ የሚችል ነው።

የሳተላይት ምስልን በጥራት ተቀብሎ ለተለያዩ ተግባራት ለማዋል የሚያስችለው መረጃ ተቀባይ ጣቢያ በተለይ ለተፋሰስና አጠቃላይ ለግብርና ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል።