የመጪው የበጋ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛ በታች ይሆናል-ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የመጪው የበጋ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛ በታች ይሆናል-ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዳማ መስከረም 12/2015/ኢዜአ/ የመጪው የበጋ ወቅት የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛ በታች እንደሚሆን የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ ።
ኢንሰቲትዩት ያለፈው የክረምት ወቅት ትንበያ ግምገማና የመጪው የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያ ላይ የሚመክር መድረክ በአዳማ እያካሄደ ነው።
የኢንሰቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት ኢንስቲትዩቱ የአየር ፀባይ ክስተቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን በመከታተል መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የአየር ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ላይ አገልግሎቶችን ለአርሶና አርብቶ አደሩ እያደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል ።
የአየር ትንበያ በጊዜ፣ በጥራትና በቦታ በማዘጋጀት ከአየር ጠባይ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ቁርኝት፣ ሊኖሩ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ስራዎችና ጎርፍን ከመከላከል አንፃር የባለፈው ክረምት የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያ የተሻለ ስራ እንዲከናወን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያ ማመላከት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በትንበያው መሰረትም ደቡብ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ክልል እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በአማካይ ከ200 ሚሊ ሊትር የማይበልጥ የዝናብ ስርጭት እንደሚያገኙም በትንበያው ተመላክቷል።
በዚህም ሊኖር የሚችለውን ከመደበኛ በታች የሆኑ የዝናብ ሁኔታን መቋቋም የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የፓስፊክ ውቂያኖስ ከመደበኛ በላይ መቀዝቀዝና የህንድ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ክፍል መሞቅ ሀገራችንን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የዝናብ ስርጭት ከመደበኛ በታች እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በተለያይ ዘርፎች ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም የሚያስችል የአየር ጠባይ ትንበያ በጥራትና በወቅቱ የማድረስ ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የአየር ትንበያ ሁኔታና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ወስደን መተግበር አለብን ያሉት አቶ ሞቱማ በተለይ ተጋላጭ የሆኑ የግብርና፣ ውሃና ኢነርጂ ላይ ከወዲሁ መስራት ይገባናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይ የሚቀርቡ የአየር ጠባይ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተንና በመተርጎም ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።