የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚሳተፍበት የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገለጸ

117

መስከረም 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚሳተፍበት የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በአካል ተገኝተው በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ ለማይችሉ ሰዎች ቪ-ሬስ (ViRace) የሚባል የቨርቹዋል መሳተፊያ አማራጭ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ሩጫው “አብሮነት መሻል ነው” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከናወን የውድድሩ አዘጋጅ ግራንድ አፍሪካን ራን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በአሜሪካ የሚገኙ ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች፣አምባሳደሮች፣ታዋቂ ሰዎችና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል።

ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ለተቋቋመው ሕብረት ለበጎ የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሚያሰራው የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል እንደሚውልና ለዚህም ከድርጅቱ ጋር የትብብር ስምምነት መፈጸሙን ገልጿል።

ግራንድ አፍሪካን ራን ከእያንዳንዱ ተመዝጋቢ ከሚገኝ ገቢ ለሕብረት ለበጎ ድጋፍ እንደሚያደርግና http://xn--www-86o.africanrun.com/ የመመዝገቢያ ገጽ ላይም የገቢ ማሰባሰቢያ ሊንክ ማዘጋጀቱን አመልክቷል።

የእገዛውን ተደራሽነት በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ለማስፋትም፣ በአካል ተገኝተው በዝግጅቱ ላይ መሳተፍ ለማይችሉ ዜጎች ቪ-ሬስ (ViRace) የሚባል የቨርቿል መተግበሪያ ወይም አፕ መዘጋጀቱን ግራንድ አፍሪካን ራን ገልጿል።

የውድድሩ አዘጋጅ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባዘጋጃቸው ሁነቶች ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጉን በመግለጫው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም