የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የጤና ሚኒስቴር

99

መስከረም 11/2022 /ኢዜአ/ በተያዘው 2015 በጀት ዓመት የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አሰግድ ሳሙኤል ለኢዜአ እንዳሉት የጤና ባለሙያዎች በየጊዜው ተለዋዋጭ ከሆነው የጤናው ዘርፍ ጋር እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ  እየተሰራ ነው።

ለዚህም በጤና ሚኒስቴር የብሄራዊ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ ሲሆን ማንኛውም ባለሙያ የሙያ ፍቃድ ከማሳደሱ በፊት ስልጠና ስለመውሰዱ ክትትል እንደሚደርግ ጠቁመዋል።

በጤና ተቋማት በተደረገ ምልከታ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ ስልጠና ያገኙ የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የእውቀትና ክህሎት ማሻሻል ማሳየታቸውን ገልፀዋል።

የጤና ተቋማት ለታካሚዎቻቸው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን በማንሳት፤ ጤና ሚኒስቴር በተያዘው በጀት ዓመት ለባለሙያዎች አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።

ሆስፒታሎች የትምህርትና የሙያ ማሳደጊያ የስልጠና ማዕከላት እንዲሆኑ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በሙከራ ደረጃ የተለዩ ሆስፒታሎችን ለመማሪያ ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በ17 ሆስፒታሎች የህክምና መሳሪያ፣ የክህሎት መለማመጃ ማዕከላትና ቤተመፃህፍት እየተሟሉ መሆኑን በመግለፅ።

ከዚህ በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት የጤና ባለሙያዎችን ማትጊያ ስርዓቶች ተቀርፀው ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁንም አንስተዋል።

የጤና ተቋማትን ለባለሙያዎች ምቹ ማድረግ፣ የተለያዩ የትምህርት እድሎች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል።

በአገር ደረጃ የተለየ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የጤና ባለሙያዎች እውቅና እንዲያገኙ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም