አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለ ሆኖ ታርመው እንዲስተካከሉ መስራት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

94

መስከረም 10/2015 (ኢዜአ) አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለ ሆኖ ታርመው እንዲስተካከሉ መስራት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባ አዳነች በልደታ ክፍለ ከተማ ከ450 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን የሕፃናት ጥፋተኞች ማቆያና የተሃድሶ ማእከል በይፋ መርቀው ከፍተዋል፡፡

May be an image of 2 people, tree and outdoors

በመዲናዋ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ልማት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው ለህፃናትና ታዳጊዎች ስብእና ግንባታ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው የሕፃናት ጥፋተኞች ማቆያና የተሃድሶ ማእከል የዚሁ ተግባር አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በማእከሉ እድሜያቸው ከ9 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ህፃናት የሚታረሙበት የማቆያና የተሃድሶ ማእከል መሆኑን ጠቁመዋል።

በጥፋቱ ማንኛውም ሰው በህግ መጠየቁ እንዳለ ሆኖ ታርሞ እንዲስተካከል መስራት ግን የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ ነው ከንቲባ አዳነች ያስረዱት።

የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሀብተማሪያም የማእከሉ ግንባታ አጠቃላይ በ20 ሺህ 186 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና 17 የተለያዩ ብሎኮችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ቤተ መጽሀፈት፣ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟሉለት ማእከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የከተማው ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣው፣ ማእከሉ 700 የሕፃናት ጥፋተኞች ማቆያና የተሃድሶ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም