ዩኒቨርሲቲዎቹ የሰሯቸው የእምቦጭ መከላከያ መሽኖች ወደ ስራ ሊገቡ ነው

62
ጎንደር መስከረም 9/2011 በጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽኖች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የአካባቢ ህግ ተግባራዊነት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ሙሉ ስሉጥ ለኢዜአ እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲዎቹ የተሰሩ ሁለት ማሽኖች በዚህ ዓመት በሙሉ አቅማቸው በጣና ሀይቅ ላይ እንቦጭን ለማስወገድ ያገለግላሉ። ይህም የማሽኖችን ቁጥር ወደ አራት ከፍ እንደሚያደርገው የገለፀጹት ቡድን መሪው ከዚህ ቀደም በአማጋ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የተገዙ ሁለት ማሽኖች 6ሺህ ሜትር ኪዩብ አረም ከሀይቁ ማስወገድ እንደቻሉ አስታውሰዋል ። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 174 ሺህ ህዝብ በማሳተፍ 3ሺህ 490 ሄክታር የሀይቁን ክፍል የሸፈነ አረም መወገዱን ገልፀዋል ። በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የለምባ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሳይ መንግስቴ ላለፉት አምስት ዓመታት ከሀይቁ ላይ አረሙን ለመከላከል የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል ። ባለፈው ዓመት አረሙን የማስወገድ ስራ በማሽን በመታገዙ ጥሩ ውጤት ተገኝቶበታል  ያሉት አርሶ አደር ሲሳይ  መንግስት የማሽኖችን ቁጥር ሊያሳድግ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም