የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ዜጎች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል- አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ

209

መስከረም 09 /2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ዜጎች ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጠየቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሃራ ሁመድ እንዲሁም ሌሎች የምክር ቤቶቹ አባላትና ሰራተኞች የተሳተፉበት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በደም ልገሳ በገንዘብ በአይነት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ በደም ልገሳው ወቅት ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በመስዋትነት ፀንታ የኖረች በመስዋትነትም ጸንታ የምትቀጥል ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያን ሉአላዊነት ሲል በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው ብለዋል።

የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላትና ሰራተኞች የደም ልገሳ መርሃ ግብር ያደረጉትም ለሰራዊቱ አለኝታነታቸውን ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ዜጎች ሁሉ በያሉበት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዘሃራ ሁመድ፤ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከደም ልገሳ በተጨማሪ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ከዜጎች የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭ ጠላቶችና ከውስጥ የጥፋት ቡድኖች ጋር እየሰራ በመሆኑ ሁላችንም በጋራ ለመመከት መነሳት አለብን ብለዋል።

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም