አሸባሪው ሕወሓትን የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው

1508

መስከረም 8 ቀን 2015(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት የከፈተውን ጦርነት የሚያወግዝና አሜሪካ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እንድትወስድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ በመካሄድ ላይ ነው።

ዋይት ሐውስ ፊት ለፊት እየተከናወነ በሚገኘው ሰልፍ ኢትዮጰያውያን፣ኤርትራውያን፣ሶማሊያውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ዳግም ወረራ የሚያወግዙና “አሜሪካ የሽብር ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን አፍራሽ ድርጊት በማውገዝ ተጠያቂ ማድረግ አለባት፣ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም ይኖርባታል” የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ነው።

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ የምትከተለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዳግም ልታጤነው እንደሚገባ የሚያሳስቡ መልዕክቶች እየተላለፉ ይገኛል።

ሰላማዊ ሰልፉን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት፣ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳጆች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል::