የሽብር ቡድኑ ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነትመንግስት ለመመከት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን -የትግራይ ክልል ተወላጆች

181

ሀረር መስከረም 8/2015 (ኢዜአ)  አሸባሪው ህወሓት የሰላም አማራጭን በመተው ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተገቢ በመሆኑ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ በሀረሪ ክልል የትግራይ ክልል ተወላጆች አስታወቁ፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ፅህፈት ቤት በክልሉ ከሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር  ዛሬ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል ፡፡

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የትግራይ ክልል ተወላጆች መንግስት አሸባሪው የህወሓት ቡድን  የሰላም አማራጭን በመተው ዳግም ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል

"ከመንግስት ጎን  በመቆም በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ እንደግፋለን" ሲሉም አስታውቀዋል ።

የትግራይ ክልል ተወላጅ አቶ ሊላይ ታደሰ የአሸባሪ ቡድኑ መሪዎች የገዛ ልጆቻቸውን በውጭ አገራት እያስተማሩ የትግራይ ድሀ እናቶች ልጆችን በጦርነት እየማገዱ መሆኑን በመግለፅ ተግባሩን አውግዘዋል ፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር  በአሸባሪ ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

 "የትግራይ ክልል ማህበረሰብ ሰላም ወዳድ ነው፤ መጥፋት ያለበትን አሸባሪ ቡድኑን  ከመንግስት ጋር በመቆም አብረን እንታገለዋለን " ብለዋል፡፡

"የትግራይ ክልል ህዝብ ጦርነት አይፈልግም" ያሉት ደግሞ በሃረር ከተማ በመምህርነት ሞያ የተሰማሩ መምህር አስፋው መስፍን ሲሆኑ "ጦርነቱ  ንጹሃን ዜጎችን እየቀጠፈ ነው"   ብለዋል፡፡

"የትግራይ ክልል  ህዝብ ስለጦርነት አስከፊነት ከማንም በላይ ያውቃል "ያሉት መምህር አሰፋ  "የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ  አሸባሪ ቡድኑ ላይ በሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ድጋፍ እናደርጋለን " ብለዋል።

"አሸባሪው የህወሃት ቡድን የኢትዮጵያ ህዝቦችን   ለመለያየት በርካታ ጥረቶችን አድርጓል" ያሉት ደግሞ አቶ ተካ አብረሃ ናቸው፤

ከኢትዮጵያ ህዝቦች እና ከአገሪቱ መንግስት ጋር በመሆን ለአገር ልማት እና ብልፅግና እንደሚሰሩ ቃል በመግባት በአገሪቱ በማንኛውም ጉዳይ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል ፡፡

"እኛ የመረጥነው ብልፅግናን እንጂ አሸባሪው ህወሃትን አይደለም"  ያሉት አቶ አጋዚ አያሌው በበኩላቸው  "አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን በነበረበት ጊዜም  የትግራይ ክልል ህዝብን አያውቀውም" ብለዋል።

ከመንግስት ጎን በመቆም ቡድኑን እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል ፡፡

"የትግራይ ህዝብ  በድህነት ነው የሚኖረው፤ ጦርነትን አይደግፍም፤ ሰላም በመፈጠሩ ቀዳሚ ተጠቃሚ የሚሆነው  በጦርነቱ ምከንያት ጨለማ ውስጥ የገባው የትግራይ ተወላጅ ነው፤  የሰላም ንግግር ሲባል ብዙ ነገር  ተስፋ አድርገን ነበር"  ብለዋል ፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ፅህፈት ቤት ምከትል  ሃላፊ አቶ አብዱል ሃኪም ኡመር መንግስት አላስፈላጊ ጦርነትና መስዋእትነት እንዳይከፈል አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል ።

"አሸባሪ ቡድኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመግፋት  በከፈተው ጦርነት የትግራይ ክልል ተወላጆችን የእሳት ማገዶ እያደረጋቸው ነው " ብለዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ እኔ ያልመራኋት አገር ትፍረስ በሚል ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር ፀረ ኢትዮጵያዊነቱን በተግባር ማረጋገጡን ጨምረው ገልጸዋል  ፡፡

"መንግስት አሁንም ለሰላም ዝግጁ ነው" ያሉት አቶ አብዱልሃኪም የትግራይ ክልል ተወላጆችን እያስጨፈጨፈ ያለውን ቡድን የትግራይ ወጣቶች  ሊቃወሙት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም