የታሪካዊ ጠላቶቻችን የዶለዶሙ የመጋዝ ጥርሶች

241

ሰሎሞን ተሰራ (ኢዜአ)

  • አሸባሪው ህወሃት ያረጀ ያፈጀ የበረሃ ቃለ መሃላውን ከቀበረበት በማውጣትና አፈሩን አራግፎ በማንሳት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር አገር የማፍረስ ሴራውን አጠናክሮ ገፍቶበታል፡፡
  • ኢትዮጵያውያን ከአባቶቻቸው በወረሱት ማንነታቸው የአሸባሪውን ህወሃትና የአጋሮቹን ሴራ በማክሸፍ አገራቸውን ከብተና ለመታደግ በጋራ የሚቆሙበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
  • ከሀዲ ማንነታቸው ገዝፎ የታሪካዊ ጠላቶቻችን መጋዝ በመሆን የሚገዘግዙንን ባንዳዎች እጅ ለመቁረጥና የመጋዙንም የዶለዶመ ጥርስ ለመነቃቀል ቆርጠን እንነሳ።

ታሪክ እንደሚያስተምረን ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ወረራዎችን በልጆቿ ተጋድሎ መክታ አልፋለች፡፡ ወረራዎቹ በውጭ ኃይሎች የተፈጸሙ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ትንኮሳዎች አገርን በከዱ የውስጥ ባንዳዎች መሪነትና አጋርነት የተፈጸሙ መሆናቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ አይናቸውን የጣሉና የነፃነት ታሪኳና ድል አድራጊነቷ እረፍት የነሳቸው ኃያላን አገራት ተደጋጋሚ የወረራ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ደረታቸውን ለጥይት የሰጡ ልጆቿ ፊት ለፊት ተጋፍጠው ህልማቸውን ከንቱ አድርገውታል፡፡ ይህን ታላቅ ጀብዱ በዶጋሊ፣ ጉንደት፣ መቅደላ፣ አድዋ፣ ጅግጅጋ የነበሩ ጀግኖች የዘመናት ቅይይር የፈጠረው ልዩነት ሳይበግራቸው በጦር ሜዳ ውሎ በተግባር አሳይተውታል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የአገዛዝ ስርአቶች የውስጥ ሽኩቻዎች ተለይተዋት የማያውቁ ሲሆን ስልጣን ለመረከብ የቋመጡ አካላት አቅማቸውን ለማፈርጠም የውጭ ኃይሎችን ድጋፍ መጠየቃቸው አይካድም፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ስልጣን ከመጡ ኃይሎች መካከል ህወሃት አንዱ ሲሆን ለ 27 አመታት አገሪቱን በፍፁም አምባገንነትና የአንድ ቡድን የበላይነት ቁም ስቅሏን ሲያሳያት ከርሞ የግፍ አገዘዙ ባንገፈገፋቸው ወጣቶች ትግል ተገፍቶ ከስልጣኑ ተወግዷል፡፡

ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ ባዘጋጀው አደረጃጀት በመጠቀም ባሻው ቦታ እንዳሻው እየገባ የፈለገውን ሲያቦካና ሲጋግር ከርሟል፡፡ ህወሃት በክልሎች የውስጥ ጉዳይ አማካሪ በሚል ሽፋን ጉዳይ አስፈጻሚዎቹን በመመደብ አንዱን ከፍ አንዱን ደግሞ አናሳ ብሎ በመሰየም ሲያሻው ደግሞ አጋር ድርጅት በማለት የድርጅቱን ድምጽ በበላይነት ሰልቅጦ በመያዝና አገር አፍራሽ ቡድኖችን በስውር በማደራጀትና የህዝቡን ህልውና በስጋት ሰንቆ በመያዝ  ዘመኑን ፈፅሟል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ የምስራቅ አፍሪካ ጠባቂ መስሎ ለመታየት ብዙ ቢዳክርም ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የሚያራምዳቸው ፖሊሲዎችና አብሮአቸው የሚሰራው እንደ አልሸባብና ሸኔ የመሰሉ አሸባሪዎችን ለተመለከተ ቡድኑ በተጨባጭ የምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱ ስጋት መሆኑን ይረዳል፡፡

ህወሃት ከመነሻው የያዘው አጀንዳ አገር ማፍረስ መሆኑን የቀደሙ መሪዎቹ ከምስረታው አንስቶ የሚከተለውን መርህ ከማስረጃ ጋር በመጥቀስ ገሃድ አውጥተውታል፡፡ ለዚህ  ማሳያ የሚሆነው "የወያኔ ታላቁ ሴራ" በማለት የቀድሞ አባላቱ አብርሃም ያየህና ገብረመድህን አርአያ በጥቅምት በ1982 ዓም ያደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡

በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ አቶ አብሃም ያየህ “ቡድኑ የተቋቋመው ለትግራይ ችግር መፍትሄ ለማስገኘት ሳይሆን በቀጥታ ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል እንድትቆራረስና ጨርሶ ህልውናዋ እንዲጠፋ የሚያደርግ ማለትም የሌሎች ቡድኖችን ጉዳይ ለማስፈጸም በመሳሪያነት ማገልገል መሆኑን ተገንዝቢያለሁ” በማለት ተናግረዋል፡፡

አቶ ገብረመድሀን አርአያ በበኩላቸው ህወሃት ቀደም ብሎ ማሌሊት በሚባልበት ወቅት ሰኔ 3 ቀን 1977 መስራች ጉባኤውን ሲያካሂድ ያወጣውን ፕሮግራም አስመልክተው እንዲህ ብለዋል ”የዚህ ፕሮግራም ስትራቴጂ አንደኛ የትግራይን መንግስት ለማቋቋም፣ ሁለተኛ ማንኛውም ብሄር አሁን ኢትዮጵያ ተብላ ከምትጠራው ውስጥ የሚኖሩ ብሄረሰቦች ተገንጥለው የራሳቸውን መንግስት ማቋቋም ይችላሉ፣ ሶስተኛ በትግራይ ውስጥ ያሉ ብሄረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ተነጥለውም የራሳቸውን መንግስት መመስረት መብት አላቸው፡፡”

በዚህ መሰረት ህወሃት ከአፈጣጠሩ አገር የማፍረስ ተልዕኮ አንግቦ መነሳቱን፣ በአጋጣሚ ስልጣን ላይ ሲወጣ ደግሞ እንደ እባብ ቆዳውን እየለዋወጠ አገር ወዳድ በመምሰል ያሻውን ሲዘረፍ፣ ሲገድልና ሲያስገድል መኖሩን አንዘነጋውም፡፡

አሁን ላይ ህወሃት ቀን ሲጎድልበት የበረሃ ቃለ መሃላውን ከቀበረበት በማውጣትና አፈሩን አራግፎ በማንሳት፣ ወደ ተፈጠረበት ዋሻ በመሸሽ፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር አገር የማፍረስ ሴራውን አጠናክሮ ገፍቶበታል፡፡

ለዚህም የህወሃት አጉራሾች የነደፉትና Command and Control Fusion Center (C2FC) ወይም “ባስማ “የተሰኘውና በሶሪያ የተሞከረው ፕሮግራም ከዜጎች እልቂት ውጭ ምንም ፋይዳ ያላስገኘውን አፍራሽ አካሄድ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

በአሜሪካና አጋር በሆኑት የአውሮፓ አገራት የተነደፈውና በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው ይህ ፕሮጀክት በሰብዓዊ ድጋፍና በዜጋ ጋዜጠኝነት ስም አገር መበታተንን ታሳቢ አድርጎ የሚተገበር ሲሆን በተለይም በህዝብ ድምጽ ስልጣን የያዘውን ህጋዊ መንግስት በጉልበት ለማውረድ ያለመ ነው፡፡

በተጨማሪም የአገር መሪዎችን በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፊት በማቆምና በሰብዓዊ መብት ጥሰት በመክሰስ አገሪቱን ማፍረስ አጀንዳው አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡ ምዕራባውያን የቀበሩትና ሰዓቱን ጠብቆ እንዲፈነዳ የታሰበው “የባስማ” ቦምብ ኢትዮጵያን በመበታተን ህዝቦቿን ለመከራ ለመዳረግ ያለመ መሆኑን በርካቶች ተስማምተውበታል፡፡

ለዚህ ደግሞ ህወሃትን በአጋፋሪነት ከፊት አስቀድመው እንደፈለጉ የሚነዷቸውን  ሸኔንና ሌሎች ነፃ አውጪ ተብዬ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎችን ከኋላ በማስከተል ለግባቸው ስኬት አገር ማተራመስ ጀምረዋል፡፡

የዲሞክራሲ አባትና እናት እኛ ነን የሚሉት ሴረኞች በጥቅምት 2013 ባወጡት ባለሰባት ገጽ ሪፖርት አሸባሪው ህወሃት የጫረው ጦርነት ወደ ኦሮሚያ ክልል ሊስፋፋ ይችላል በሚል በማር የተለወሰ ሬት የመሰለ መላምታቸውን አስቀምጠውበታል፡፡ ይህ ሪፖርት በጥንቃቄ ለተመረጡ የአውሮፓ ህብረት አባላት የተላከ ሲሆን በመቀጠል ለህብረቱ ምክር ቤት ቀርቦ በምስጢር ምክክር ተደርጎበታል፡፡

ሪፖርቱ የተለያዩ ሀገራት ግጭቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው የሚያትት ሲሆን በቀጣይ የጅቡቲን ኮሪደር በመዝጋት የኢትዮጵያን እጅ መጥምዘዝ እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን ሰላማዊ በሚመስል መንገድ በመከፋፈልና ታጣቂዎችን ህወሃትን ጨምሮ ጥምር መንግስት እንዲመሰርቱ በማድረግ በቀጣይ የራሳቸውን መብት በራሳቸው ይወስኑ በሚል ማደናገሪያ አገሪቱን የመበታተን ሴራ መንደፋቸውን ሰነዱ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የዘየዱት መላ ግቡ አገሪቱን እንደ ዩጎዝላቪያ ሰላማዊ በሚመስል ነገር ግን ውስጡ በተዳፈነ የእሳት አረንቋ ውስጥ በማስገባት እንደፈለጉ መጋለብ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያንን አፅንቶ ያቆማቸው ደመ መራር ማንነታቸው የህወሃትንና የአጋሮቹን ሴራ በማክሸፍ አገራቸውን ከመበታተንና ከውርደት እንዲታደጉ አስችሏቸዋል፡፡

ቅደመ አያቶቻቸው፡ አያቶቻቸውና አባቶቻቸው በህብረት በመቆም፣ በጦርና በጎራዴ ያንበረከኩት ወራሪ ኃይል በእጅ አዙር ለዳግም ወረራ ቢሰለፍም አርበኝነቱን የወረሱት ልጆቻቸው በደም መስዋዕትነት ዳግም ጠላትን አዋርደል፡፡

ፊት ለፊት ኢትዮጵያውያንን መጋፈጥ የማይደፍሩት ወራሪዎች Command and Control Fusion Center (C2FC) በተሰኘው ፕሮግራማቸው አማካሪ፣ አመቻች፣ የአቅም ግንባታና የስለላ ዘርፍ አደረጃጀቶችን በመመስረት ህልማቸውን ለማሳካት ከህወሃት ጋር አብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ፕሮግራሙ በዋናነት አቅም ግንባታ በሚለው ዘርፍ የመረጃ ዘርፉን በስፋት በማደራጀት ህወሃት የከፈተውን ወረራ በበላይነት እየቋጨ መሆኑን ማራገብ፣ በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ከንፋስ በፈጠነ መልኩ ማሰራጨትን ታላሚ ያደረገ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተከፋይ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ድረ ገፆችን በስፋት በመክፈት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ማጧጧፍ የግባቸው ማጠንጠኛ ነው፡፡ በተለይ መቀመጫቸውን ኬኒያ ያደረጉ የመንግስት ተቃዋሚዎችን በስለላ ተቋማት አጋርነት በማደራጀት መጠቀም እንደሚገባ ይጠቅሳሉ፡፡

በቀጣይነት ቀዳዳዎችን ማስፋት በሚለው መርሆዋቸው ታዋቂ መገናኛ ብዙሃንን  (ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ፣ ሮይተርስ ወዘተ)፣ ጋዜጠኞችን፣ ግለሰቦችን፣ ምሁራንን፣ ምዕራብ ዘመም የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎችን፣ የዲሞክራሲ መብት አቀንቃኞችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በጄኦፖለቲካ ተረኮቹ የሚታወቀውን ስትራትፎር የተባለውን ተቋም በመጠቀም አገሪቱን ማተራመስ የሚል ግብ አስቀምጠው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

የዚህ ሁሉ ግብ ማስፈጸሚያ መሳሪያቸው ደግሞ ከፍጥረቱ ኢትዮጵያን የማተራመስ አላማ አንግቦ የተመሰረተው አሸባሪው የህወሃት ቡድን ነው፡፡ የባስማ ፕሮጀክት ህወሃትን መሰረት በማድረግ ትግራይን የተመለከቱ ጥሬ ሃቆችን በመሰብሰብና አዛብቶ በመተንተን በመላው አለም ላስቀመጣቸው ሸቃጭ ጋዜጠኞች በመበተን በተጠናና ቅፅበታዊ በሆነ መንገድ  አለም እንዲጋራው ያደርጋል፡፡

በተቃራኒው የተጭበረበሩ አድራሻዎች በሚል ሽፋን ለኢትዮጵያ እውነት የሚሞግቱ ሰዎች የማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲዘጉ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ገዳይ በሚለው የጋዜጠኝነት መርህ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሆን ብሎ ማሰራጨት ውሸት መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ዝም ብሎ ማለፍ የህወሃትና አጋሮቹ የሽብር ማስፈጸሚያ ስልት አካል ናቸው፡፡

ከጥቅምት 2013 አንስቶ መንግስት ፈፅሟቸዋል በሚል በነዚሁ አካላት የሚሰራጩ ሃሰተኛ ዘገባዎች ለህወሃት የልብ ልብ ቢሰጡትም ይህ ድጋፍ መሬት ላይ ወርዶ ቆፍጣናውን የኢትየጵያ ህዝብና የመከላከያ ሰራዊት ሊበግረው አልቻለም፡፡ ለአብነትም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሐምሌ 2013 ለእይታ ያበቃው ፎቶ የያዘው መልዕክት የተሳሳተ ነበር፡፡

ህወሃት በጀመረው ወረራ የተፈጠረውን ቀውስና ቀዳዳ ተከትሎ ምዕራባውያን ህልመኞች፣ አፍቃሪ ህወሃቶች፣ አለም አቀፍ የህግ ምሁራን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ተብዬዎች ከፍተኛ የአገር መሪዎችን  በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት አቁመው በመክሰስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ውጥን ይዘው እየቃዡ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተያዘው ዕቅድ በህወሃት ወረራ ከተጀመረ አንስቶ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በርካታ የመከራ ገፈቶችን እንዲቀምሱ ቢደረጉም ለአገራቸው ሉዓላዊነት በፅናት ቆመዋል፡፡

ወረራውን ተከትሎ ተፈጸሙ የተባሉ ጥፋቶችን የመረመሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ቢሮ በጋራ ያወጡትን ሪፖርት በአንፃራዊነት የተቀበለው የኢትዮጵያ መንግስት በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል፡፡

በዚሀም የመከላከያ ሰራዊት ፍርድ ቤት በማቋቋም በጥፋት ተግባሩ ላይ ተሰማርተው በተገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ አስፈላጊው ቅጣት እንዲጣልባቸው አድርጓል፡፡

በአንጻሩ በህወሃት በኩል በጥፋት ተግባሩ ላይ የተሰማሩ የቡድኑ መሪዎችና አባላቱ ቅንጣት ግሳፄ ሳይደርስባቸው በአለሁ ባይ ቀላቢዎቻቸው ትከሻ ላይ ቆመው ዳግም ወረራ ፈጽመዋል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ጉድለት ቢኖረውም መንግስት በአዎንታዊነት በመቀበልና የሰላም አማራጭ በማቅረብ ለምክክር ዝግጁ መሆኑን በገለጸበት በዚህ ወቅት ህወሃት ዳግም ወረራ መፈጸሙ ይታወቃል። ነገር ግን የኢትዮጵያን ጸንቶ መቆም የማይሹ አካላት አሸባሪውን ቡድን ከማውገዝና ስርአት ከማስያዝ ይልቅ የኢትዮጵያን መንግስት የሚወነጅል ሪፖርት ለማውጣት ሽር ጉድ እያለ ይገኛል፡፡

ይህ የሚያሳየው በአራቱም ማዕዘን በመቆም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሰለፉት አካላት አገሪቱ ካልተበታተነችና እንደፈለጉ የሚዘውሩት መንግስት መንበሩን ካልጨበጠ እንቅልፍ አንደማይወስዳቸው ነው፡፡

እናም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሸረበብንን ጊዜ የማይሰጥ ሴራ በመረዳት በጋራ ለአገራችን ህልውና መከበር የሚጠበቅብንን ኃላፊነት መወጣትና መስዋዕትነት መክፈል ትንሿ ግዴታችን መሆኗን አንዘንጋ፡፡

በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉና አብሮነታችንን የሚንዱ፣ መንግስትን የሚያጠለሹ፣ የብሄር ልዩነትን የሚሰብኩ፣ ግጭትን የሚጭሩ መልዕክቶችንና መልዕክቱን የሚያስተላለፉ ከንቱዎችን ልንታገላቸው ይገባል፡፡

የምንታገለው ለመንግስት ህልውና ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ህልውና መሆኑን አንዘንጋ፣ ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን በመሆኗ ሲያምርባት የሚያምርብን ስትጎሳቆል አብረናት የምንጎሳቆል ነን፡፡

ነገር ግን በሴረኞች ተንኮል አገራችን ከፈረሰች የሁላችንም መጨረሻ አገር አልባ ከሆኑ ሰዎች የተለየ ስለማይሆን ለሁሉም ነገር እንዘጋጅ። ከሀዲ ማንነታቸው ገዝፎ የታሪካዊ ጠላቶቻችን መጋዝ በመሆን የሚገዘግዙንን ባንዳዎች እጅ ለመቁረጥና የመጋዙንም የዶለዶመ ጥርስ ለመነቃቀል ቆርጠን እንነሳ። ከአባቶቻችን የተረከብናትን ነጻ አገር በተባበረ ክንድ ከነክብሯ ጠብቀን ለትውልድ ለማቆየት እንሰለፍ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም