ከሰሞኑ በዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከኦሮሞ ባህል ያፈነገጠ ነው...አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች

65
ቡራዩ መስከረም  9/2011 አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ከሰሞኑ በቡራዩና  አካባቢው የተፈጸመው ጥቃት "ከኦሮሞ ባህል ያፈነገጠና አስነዋሪ ነው" መሆኑን ተናገሩ። የቡራዩ ከተማ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች እንዳሉት የኦሮሞ ህዝብ በጉዲፈቻ፣ በሞጋሳና በተለያዩ ስርዓቶች ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን እና ልጆችን እንደራሳቸው ልጅ በማየት የሚያሳድጉና የሚያኖሩ እንጂ የሚገድሉ አይደሉም ብለዋል። በመሆኑም በከተማዋ የተፈጠረው ችግር የኦሮሞን ህዝብ በእጅጉ ያሳዘነና የአካባቢውን ህዝብ የማይወክል ድርጊት ነው በማለት ተናግረዋል። "የድርጊቱ ፈጻሚዎች ቄሮን መስለው" አደጋ ያስከተሉ በመሆናቸው መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት። በዚህ ሂደት የተፈናቀሉ ዜጎች በአፋጣኝ ወደቄያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ስራዎች ተጀምረዋል ሲሉ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ˝አባ ገዳ ተሬሳ ኢደቲ በሰጡት አስተያየት  ቄሮን መስሎ በመግባት  ወንድሞቻችን በመደብደብ በመግደል፣ ከቤት የማባረር ድርጊት  የኦሮሞን ህዝብንና  ቄሮን አይወክልም፤ የአሮሞ ህዝብ ሌሎች ወንድሞቹን አይጠላም አቃፊ ነው፤ አብሮ ተወልዶና ተጋብቶ የሚኖር ህዝብ ነው፤ የተለየ ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይህን የፈጸሙት˝  ብለዋል፡፡ ለብዙ ጊዜ አብረን የኖርን የተዋለድን ዜጎች በመሆናችን የተፈናቀሉ ወገኖቻች በአፋጣኝ እንዲመለሱ የተለያዩ ስራዎችን መጀመራቸውን የገለጹት ደሞ  አቶ ተረፈ ዓለማየሁ ናቸው  ፡፡ ከቡራዩ ከተማ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ከአባ ገዳዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ኮሚቴ በማዋቀር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም