ብአዴን ለውጡን የሚያስቀጥሉ አዳዲስ አመራሮችን በማምጣት ለጠንካራ ትግል መዘጋጀቱን አስታወቀ

1143

ባህርዳር መስከረም 9/2011 የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በ12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ለውጡን ተረድተው የሚመሩ አዳዲስ አመራሮችን በማምጣት ጠንካራ የትግል ድርጅት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለውን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አስታወቀ።

“የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከመስከረም 17 እስከ 21 ቀን 2011 በባህር ዳር ከተማ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ብናልፍ አንዷላም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በጉባኤው ለውጡን በትክክለኛ መንገድ እንዲመራ ጥልቀት ያለው ውይይት በማድረግ ግልፅ አቅጣጫ ይቀመጣል።

አሁን በሃገራችንም ሆነ በክልላችን የመጣው አዲስ ለውጥ የህዝቡን ተስፋ ያለመለመ መሆኑን አመልክተው፤ “ይህን በመምራት፣ በማደራጀትና በማስተባበር ብአዴን ሚናውን የሚወጣበትን ስልታዊ አካሄድ ይቀይሳል” ብለዋል።

ህዝቡ በለውጡ በርካታ መሰረታዊ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና መሰል ጥያቄዎች እንዲመለሱለት ብአዴን አሰራሮችን ፈትሾ በማስተካከል አቅጣጫ እንደሚነድፍ ተናግረዋል።

በጉባኤውም በህዝብ፣ በድርጅቱና በወጣቱ እየተመራ የመጣውን የለውጥ እንቅስቃሴ በዋናነት በመገምገም ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ የሚጠነክሩበት ደካማ ጎኖች ደግሞ የሚስተካከሉበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የትግሉ ባህሪ ወቅቱን ያገናዘበ የወደፊቱን ትግል ያመለካተ አቅጣጫን በመከተል የድርጅቱን ስያሜና አርማም ገምግሞ እንደሚቀይርም አስታውቀዋል።

ህገ-ደንቦች፣ ፕሮግራሞችንና ሌሎች አሰራሮች ተፈትሸው ማስተካከያ ይደረጋልም ብለዋል።

እንዲሁም ያለፉት ሦስት ዓመታት የልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና የፀጥታ የእቅድ አፈፃፀሞችን  በመገምገምም ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየት ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የርብርብ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ተናግረዋል።

በኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የደረጋል ያሉት አቶ ብናልፍ ድርጅቱን በብቃት የሚመሩ የማዕካለዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫም እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ብአዴን ህዝባዊ ሃላፊነቱን እንደያዘ እንዲቀጥልና የአማራ ክልልን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዘመኑ የደረሰበትን የአመራር ጥበብ የተካኑ ብቁና ወጣት አመራሮችን በየደረጃው ግንባር ቀደም አድረጎ ማምጣት ከጉባኤው የሚጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል።

ከመስከረም 17 እስከ 21 በሚካሄደው ጉባኤም በድምፅና ያለድምፅ የሚሰታፉ አባላት፣ ታዛቢዎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ወጣቶች ይሳተፋሉ።

ጉባኤው ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ግልፅ ውይይት የሚደረግበት በአጀንዳዎች ዙሪያ መግባባት የሚደረስበት እንደሚሆንም አመልክተዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ አልማሃል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ማንነትን መሰረት ተደርጎ የደረሰውን ጥቃት የክልሉ መንግስት እንደሚያወግዝ ጠቁመው፤ አጥፊዎቹ በህግ እንዲጠየቁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ  ይደረጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባና አካባቢው የተካሄደው ጥቃትም ዘመኑ የደረሰበትን የስልጣኔ ጊዜ የማይመጥን ተግባር በመሆኑ ክልሉ እንደሚያወግዘው ጠቁመው፤ አጥፊዎቹ በህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንሚሰጣቸውም ገልፀዋል።