የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ፣ የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ

152
ቡራዩ መስከረም 9/2011 የቡራዩ ከተማ ፖሊስ በተለያዩ ቀበሌዎች የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ፣ የጦር መሳሪያ፣ ገንዘብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ። በግለሰቦች መኖሪያ ቤትና በተሸከርካሪዎች ላይ በተደረገ ፍተሻ የአዲስ አበባ ፖሊስና የአገር መከላከያ ሰራዊት ደንብ ልብስ፣ 3 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 5 ሽጉጥ፣ የተለያዩ ህገወጥ ማህተሞች፣ 45 ሺህ ብርና ሌሎች ድምጽ አልባ መሳሪያዎች ተይዘዋል። ግጭቱን ለማስተባበር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ቪትስ መኪናዎች ከነአሽከርካሪያቸው መያዙን የከተማዋ ፖሊስ ጠቁሟል። የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደረጀ ባይሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቡራዩና አካባቢዋ በደረሰውን ጥቃት የተጠረጠሩ ሰዎች ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ የተናገሩት አዛዡ በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። ፖሊስ የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት ከወጣቶች፣ ከአድማ በታኝ ፖሊስና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ችግሩን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎች ሰርቷል። እስከ ትናንት ድረስ በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ መድረሱን ተናግረዋል። በደረሰው ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖች ቢኖሩም ድርጊቱ የኦሮሞ ህዝብ ተግባር ሳይሆን የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀጥል የሚፈልጉ ሃይሎች ተግባር እንደሆነ ኮማንደር ደረጀ ገልጸዋል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላት ያለው ኮሚቴ ተቋቋሞ እየተሰራ መሆኑንና ህብረተሰቡም የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፖሊስ አዛዡ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም