የ “ያ ሆዴ” በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

208

ሆሳዕና፣ መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) የሀዲያ ብሄር የዘመን መለወጫ የሆነውን የ “ያ ሆዴ” በዓል በደምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

የሀዲያ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ርስቱ ለኢዜአ እንዳሉት የሀዲያ ብሄር የዘመን መለወጫ የሆነው የ”ያ ሆዴ” በዓል የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴትን የሚያጠናክር ነው።

የ “ያ ሆዴ” በዓል እሩቅ የሚኖር ቤተሰብ ተሰባስበው በጋራ የሚያከብሩት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የአንድነት በዓል መሆኑን ገልጸው የበዓሉ መከበር በብሄሩ ተወላጆች ዘንድ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዘመን መሸጋገሪያ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑን አብራርተዋል።

በአሉ የእርቅና የሰላም፣ ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ላሸጋገረው ፈጣሪ በንጹህ ልቦና ምስጋና የሚቀርብበት፤ ለቀጣይ ዘመን ጠንክሮ ለመስራትና ድህነትን ለማሸነፍ የሚመከርበት ጭምር በመሆኑ በዓሉ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

በመሆኑም በዓሉ ካለው የአብሮነት የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ለማጠናከር አስተዋጾኦው ከፍተኛ በመሆኑ በደማቅ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን ከሌሎች የአጎራባች አከባቢ እንግዶችንና ምሁራን በመጋበዝ በቅንጅት ለማክበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዓሉ ያለው እሴቶች ሳይበረዙና ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ የተከናወኑ የምርምር ስራዎች ተግባራዊ ለማድረግና በታሪክ የመሰነድ ጨምሮ የማስረጽ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

የሀድያ ባህል ሽማግሌ አበጋዝ መንግሥቱ አባቢያ በበኩላቸው “ያሆዴ” በዓል ዓመት ተጠብቆ በመሰባሰብ በአንድነት የሚከበር በመሆኑ አብሮነት እንዲጠናከር በማድረግና ለሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጾ አለው።

በዓሉ ከአሮጌው ወደአዲሱ ዓመት መሸጋገር መሆኑን ለማብሰር የተጣላ ታርቆ በአዲስ አዕምሮና በንጹህ ህሊና ወደልማት የሚገባበት በልዩ ድምቀት የሚከበር ነው ብለዋል ።

የብሄሩ ተወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጁ ምግቦችን ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በመካፈል በጋራ የሚያከብሩት የአብሮነት በዓል መሆኑን ጠቁመው በልዩ ጉጉት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል ።

"ለሀገራችን የሰላም፣ የብልጽግናና ወደ ከፍታ ማማ የምትደርስበት እንዲሆን በሽማግሌዎች ፀሎትና ምረቃት ይከናወንበታል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከቴክኖሎጂና ከውጭ ባህሎች ተጽዕኖ የተነሳ ሀገር በቀል ባህሎች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን እየተገነዘብን ነው" ያሉት የሀዲያ የሀገር ሽማግሌው ያሆዴ በመጤ ባህሎች ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ህዝባዊ መሰረቱ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ 14 ቀን 2015 ድረስ በተለያዩ ኩነቶች እንደሚከበር ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም