በእንስሳት ዘርፍ የተካሄዱ ምርምሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እየሰራሁ ነው….ማህበሩ

144

ሀዋሳ መስከረም 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ በእንስሳት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በዘርፉ የተካሄዱ ምርምሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ።

30ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር ዓመታዊ  ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት  ፕሮፌሰር ዳንኤል ተመስገን እንደገለጹት አሁን ላይ በሀገሪቱ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርት የገበያ ፍላጎት በእጅጉ እያየለ መጥቷል።

ፍላጎቱን በማሟላትና በማጣጣም  ዘርፉ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዲያበረክት የሁሉንም አካላት  ጥረትና ተሳትፎ እንደሚፈልግ አስረደተዋል።

በተለይ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ የሚታዩ ማነቆዎች እንዲፈቱ፣ ዘመናዊ አረባብና የአመራረት ሂደት እንዲሳለጥ፣ ቴክኖሎጂ እና የግብዓት አቅርቦት እንዲሻሻልና እንዲስፋፋ ማህበሩ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ረገድ የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚረዱ ምርምርና ጥናት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው"ለዚህም ማህበሩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በእቅርቦት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ሣይንሳዊ ምርምሮች እንዲካሄዱና በምሁራን እንዲገመገሙ፣ወቅታዊና አዳዲስ የዘርፉ የምርምር ውጤቶች ታትመው ለተጠቃሚዎች እንዲሰራጩ ማህበሩ በቅርበት እየደገፈ እንደሚገኝ አውስተዋል።

በእንስሳት እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  በእንስሳት ዘርፍ የተካሄዱ ምርምሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ዳንኤል አክለው የማህበሩ አባላት በምርምር ልማት እንዲሳተፉና በልማቱ እንዲሰማሩ፣እስከ አርቢው ማህበረሰብ የእውቀት ሽግግር እንዲሰርፅ በተለያየ መንገድ እያበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።

ለሶስት ቀን በተዘጋጀው መድረክ ከ70 በላይ በእንስሳት ሀብት ልማት፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ በላው ፋይዳ ላይ ያተኮሩ የምርምር ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው አስታውቀዋል።
ከጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት በሰጡት አስተያየት የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሙያ ማህበራትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር 30 ዓመት ያህል የካበተ ልምድ ያለውና በተለይ መስክ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የጎላ አስተዋጾ ማበርከቱን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን የእንስሳት ሀብት ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት በመንደፍ በተመረጡ 58 ወረዳዎች ውስጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው "በዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ጭምር ለማስረጽ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ዶክተር ቶማስ አክለው ማህበሩ የሰውን ልጅ የምግብ ፍላጎት እንዴት ከእንስሳት በሚገኝ ውጤት ዘለቄታዊ ማድረግ እንደሚቻል ዋነኛ ስራው አድርጎ መስራት እንዲችል በጉባኤው ግብዓት እንደሚገኝበት አውሰተዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ  ዩኒቨርስቲው በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ቀዳሚ የትኩረት መስክ በማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በትምህርቱ መስክ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ባለሙያዎችን እያስተማረ መሆኑን ጠቁመው "በምርምር ረገድም በርካታ ጥናቶችን በማካሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ለህትመት አብቅቷል" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት የምርምር ግኝቶችን ወደ ማህበረሰቡ ከማድረስ አንፃር ከፍተኛ የስጋና የወተት ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን ዶሮ፣ አሣ፣ በጎችና ፍየሎችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማሰራጨት ተጠቃሚ አድርጓል።

በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰት የእንስሳት መኖ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ለተጠቃሚው ለማስተዋወቅና ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው " በስራውም ውጤት ተገኝቷል" ብለዋል።
በዛሬው የጉባዔው ውሎ  ለማህበሩ ምስረታና ስራ ከፍተኛ አስተዋጾ ላደረጉ ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን በሶስት ቀን ቆይታውም በእንስሳት ሀብትና እርባታ ላይ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ታውቋል።
በጉባኤው ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከባለድርሻዎች የተውጣጡ አካላት፣ ምሁራን፣ የእንሰሳት የጤና ባለሙያዎችና የልማት አጋሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም