የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለሚያስከብረው ሰራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጋችን ይቀጥላል

177

መስከረም 5/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለሚያስከብረው ሰራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጋችን ይቀጥላል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ተናገሩ።

የሚኒስቴሩ አመራርና ሠራተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነታቸውን ለማሳየት የደም ልገሳ አድርገዋል።

ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፤ የአገር መከታ ለሆነው ሰራዊት ደም በመለገሳችን ተደስተናል ብለዋል።

"የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለሚያስከብረው ሰራዊት ከደም ልገሳ ባለፈ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ አብሮነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

አገሪቱ እያጋጠማት ያለውን ፈተና በአሸናፊነት ለመቀልበስ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ደም በመለገስ መከላከያ ሰራዊቱን ማበረታታትና አጋር መሆን ይገባል ነው ያሉት።

የዜጎችን የምግብ ዋሰትናን ከማረጋገጥ አኳያ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው መከላከያ ሰራዊቱ በግንባር የሚያደርገውን ተጋድሎ የተቋሙ ሰራተኞች በልማቱ እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

ከደም ልገሳው ባሻገር በሌሎች የድጋፍና መሰል ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተዋል።

ለመከላከያ ሰራዊቱና ለጥምር ኃይሉ እየከፈለ ካለው መስእዋትነት አንጻር ደም መለገስ ትንሹ ግደታችን ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም