የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ማነቃቃት አስችሏል

246

መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ማነቃቃት መቻሉን የኢትዮጵያ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሃብት ቢኖራትም ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች የምታገኘው ገቢ ግን አነስተኛ ነው፡፡

ለዚህም ደግሞ የብድር አቅርቦት፣የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የግብዓት የጥራት መጎደል በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪ የኮቪድ ወረርሽኝና የዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ መቀያየር በዘርፉ ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው ይጠቀሳል፡፡

በቅርቡም በተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት ዘርፉ መነቃቃት እያሳየ መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርሀኑ ስርጀቦ ፤ የ”ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ የቆዳና የቆዳ ውጤት ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዲጀምሩ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ተዘግቶ የቆየው የጆርጁ ሹ የቆዳ ፋብሪካ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ከ50 በመቶ በላይ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ሁዋጂያን እና ሌላኛው ዮውባንግ ፋብካዎች በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡

ይህም በተለይ ከውጭ የሚገቡ የቆዳ ውጤቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የጠቀሱት፡፡

የንቅናቄው መጀመር በአዲስ አበባ የትምህርት ቤት ጫማና ቦርሳ በስፋት ለማቅረብ ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል።፡፡

በተጨማሪ ለጸጥታ አካላት ጫማና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ያስቻለ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ”ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ”  በአስር ዓመት ስትራቴጅክ እቅዱ ላይ በዘርፉ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካተ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችል አደረጃጀት በመዘርጋት ተግባራዊ ማደረግ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ 179 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ እድል የፈጠረ መሆኑሙ ተመላክቷል፡፡

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 50 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም