አማርኛን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ የሚያግዝ ስራ እየተሰራ ነው

1174

ባህር ዳር መስከረም 03 /2015 (ኢዜአ) ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከጀርመኑ ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረው ግንኙነት አማርኛን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ ያግዛል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገለጹ።

“የአማርኛ ቋንቋና የኢትዮጵያ ባህል ጥናት ዓለም አቀፍ ስልጠና” ዛሬ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።

ለሁለት ሳምንታት በሚቆየው በእዚህ ስልጠና በሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ እስራኤል እና ሶሪያ ሀገራት ተማሪዎች እየተሳተፉ ነው።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በስልጠና ማስጀመሪያ ላይ እንዳሉት፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትምህርት እና በጥናትና ምርምር ሥራዎች ተባብሮ እየሰራ ነው።

ከሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተጀመረው ግንኙነት የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ገልጸዋል።

“በተጨማሪም የአማርኛ ቋንቋን በጥናትና ምርምር በማሳደግ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል” ብለዋል።

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መጥተው በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተማሪዎችም በቆይታቸው የአማርኛ ቋንቋን ከመማር ባለፈ የአካባቢውን ባህል እንዲያውቁ ማድረግ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት የራሱ አስተዋጾ እንዳለው ተናግረዋል።

ሰልጣኞች ከትምህርቱ ጎን ለጎን በጣና ሐይቅ የሚገኙ ገደማትን፣ የጢስ ዓባይ ፏፏቴን፣ በባህር ዳር ያሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በመጎብኘት እውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

በጀርመን አገር የሚገኘው የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ ዶክተር ጌቴ ገላዬ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ምዕራባውያን የግእዝና አማርኛ ቋንቋን ስርዓተ ትምህርት ቀርጸው ከ100 ዓመታት በላይ አስተምረዋል።

ለእዚህም ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ 100ኛ ዓመቱን በቅርቡ ሲያከብር የአማርኛ ቋንቋ በጀርመን እንደ ትምህርት የተሰጠበትን 100ኛ ዓመት አብሮ ማክበሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ለዚህም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደባህር ዳር በማምጣት በተግባር የታገዘ የአጭር ጊዜ ትምህርታዊ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ጠቁመዋል።

የጀርመን ምሁራን የባህር ዳር ከተማን የመጀመሪያው ማስተር ፕላን በመስራት ከተማዋ አሁን ለደረሰችበት እድገት አሻራቸውን አሳርፈዋል” ያሉት ዶክተር ጌቴ፣ በቀጣይም ግንኙነቱን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂውማኒትስ ፋኩልቲ ዲን ዶክተር ዋልተንጉስ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ታላቅ ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።

የአማርኛ ቋንቋን በምርምርና ጥናት በማዳበር እድገቱን ለማፋጠን መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

“ለዚህም ወደባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመጡት የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና መስጠትና የአካባቢውን ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና ቅርስ እንዲገነዘቡ ማድረጉ አጋዥ ነው” ብለዋል።

ዶክተር ዋልተንጉስ በስልጠናው ተማሪዎቹ የአማርኛ ስነ ቃሎችንና አባባሎችን እንዲያውቁ፣ አጫጭር ንግግሮችን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡና ሌሎች ከማህበረሰቡ እሴት ጋር ተያያዥ የሆኑ ሥራዎችን መከናወን የሚያስችላቸው መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ተማሪዎቹ በቆይታቸው የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ይደረጋል።በባህል ምሽቶችን እና በኪነ ጥበብ መድረኮች በመታደም ተጨማሪ እውቀት እንዲቀስሙ የሚደረግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

“ሰልጣኞቹ መጪውን የመስቀል በዓል ከህዝቡ ጋር አብረው በማክበር የኢትዮጵያውያንን የዳበረ እሴት እንዲገነዘቡ ማድረግ ይገባል” ያሉት አቶ ጣሂር፣ የሰልጣኞቹ ቆይታ የተሳካ እንዲሆንም ቢሮው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።